“ህፃናትን ለዕኩይ ተግባር መጠቀሚያ ማድረግ አይገባም” አቶ ከድር ጁሀር የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ

    የድሬዳዋ አስተዳደር ሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ቢሮ “ሰብዓዊነትና የላቀ ትኩረት ለህጻናት ደህንነት” በሚል መሪ ቃል የአፍሪካ ህጻናት ቀንን አክብሯል፡፡

         በአፍሪካ ለ29ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ28ኛ ጊዜ በሚከበረው የአፍሪካ ህፃናት ቀን ፕሮግራም ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ለህፃናቱ መልዕክት ያስተላለፉት የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሀር እንደተናገሩት ህፃናትን ለዕኩይ ተግባር መጠቀሚያ ማድረግ እንደማይገባ በመግለፅ ህፃናት ነገ ሀገር ተረካቢ በመሆናቸው መንግስትና ባለድርሻ አካላት ቅንጅታችንን በማጠናከር ኃላፊነታችን መወጣት አለብን ብለዋል፡፡

         ምክትል ከንቲባው አክለውም ከሱስ የጸዳ የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጋ እንዲኖር ሁሉም ዜጋ የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

     

         ቀኑን በማስመልከት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር የሴቶችና ህፃናት ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ እንደተናገሩት ህጻናትን የመንከባከብና የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጋ እንዲሆኑ የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም ህብረተሰብ ድርሻ ነው ብለዋል፡፡

         ኃላፊዋ ከዚህም ጋር በማያያዝ በከተማዋ ጎዳና ላይ ወጥተው የሚገኙ ከ800 በላይ ህጻናትን ወደ ማቆያ ለማስገባት መዘጋጀታቸውን በመግለፅ፤ ህጻናት በሱስ ተጠምደው አላስፈላጊ ድርጊት ሲያደርጉ መከላከል ላይ ባለድርሻ አካላትም ሆነ ነዋሪው ማህበረሰብ የድርሻቸውን እንዲወጣ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

         የህጻናት ፓርላማ ፕሬዝዳንት ተማሪ ሩት ታከለ በበዓሉ ስነ-ስርዓት ባስተላለፈችው መልዕክት ሀገራችን ለህጻናት ትኩረት ሰጥታ በተባበሩት የህጻናት ኮንቬንሽንና የአፍሪካ ህጻናት ቻርተር ከመፈራረም በተጨማሪ በህገ መንግስቱና በቤተሰብ ህጉ የህጻናት ፖሊሲ በመቅረጽ የተለያዩ ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩልን ቢደረግም ተፈፃሚነቱ ላይ ክፍተቶች በመኖራቸው የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና የአስተዳደሩ አመራሮች የድርሻቸውን እንዲያደርጉ ስትል ጥሪ አቅርባለች፡፡

    Leave a Reply

    Your email address will not be published. Required fields are marked *