ለተፈናቃዮች 10.5 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል

    ከሰኔ 7 እስከ 21 ድረስ በአስተዳደራችን ድሬዳዋ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ላይ ለተፈናቀሉ ዜጎች ማቋቋሚያ የሚውል 10.5 ሚሊዮን ብር ከነዋሪው ህብረተሰብ ለማሰባሰብ የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ለማዘጋጀት ማቀዱን የድሬዳዋ አስተዳደር ቀይ መስቀል ማህበር አስታወቀ፡፡

     

         ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገራችን በተከሰተ ጊዜያዊ ግጭት ሳቢያ ከ3 ሚሊየን በላይ ኢትዮጲያውያን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ቤት ንብረታቸውን ትተው ከተፈናቀሉት 3 ሚሊየን ዜጎች ውስጥ 2 ሚሊየኑ ወደ ቀያቸው የመመለስ ስራ በመንግስትና ህዝብ ከፍተኛ ጥረት የተሳካ ሲሆን አሁንም ድረስ  1 ሚሊየን የሚሆኑት በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ናቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ አቅመ ደካሞች፣ ሴቶችና ህጻናት ይገኙበታል፡፡

         እነዚህን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም ከ40 ቢሊየን ብር በላይ ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም ለወገን ደራሽ ወገን ነው በሚል ለወገኖቻችን መልሶ ማቋቋሚ የሚውል 1 ቢሊየን ብር እንደ ሀገር ለመሰብሰብ የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ለማዘጋጀት መታቀዱን አቶ ከተማ ተሰማ የድሬዳዋ አስተዳደር ቀይ መስቀል ማህበር ኃላፊ ተወካይ ገልፀዋል፡፡

         በዚህ የገቢ አሰባሰብ መንግስታዊ ተቋማት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ሲቪል ሰርቫንቱና የአስተዳደሩ ሰራተኞች እንደ ድሬዳዋ አስተዳደር የተዘጋጀውን 7000 ኩፖን አንዱን በ1000 ብር በመግዛት የወገን ሀለኝታነታቸውን እንዲያረጋግጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡

         አቶ ከተማ ባስተላለፉት መልዕክት ኩፖኑ በቀይ መስቀል ቢሮ በማንኛውም የስራ ሰዓት ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ የሚገኝ ሲሆን በየተቋማቱ በመዞር እንዲሁም ለቅስቀሳ በተዘጋጀ መኪና ከተማውን በመዞር እንደሚሸጥ ገልፀዋል፡፡ ኩፖኑ በሰብአዊነት ተፈናቃዮችን ለመርዳት በነፃ የሚገዛ እንጂ እጣ ያለው ወይም ሽልማት የሚገኝበት አለመሆኑን በመግለፅ ለብቻው 1000 ብር ወይም 2000 ብር አውጥቶ የመግዛት አቅም የሌለው ሰው በጋራ በመሆን አዋጥቶ መግዛት እንደሚችልም አቶ ተሰማ ተናግረዋል፡፡

    Leave a Reply

    Your email address will not be published. Required fields are marked *