የዓለም ጤና ድርጅት/WHO ድሬዳዋ ቅርንጫፍ በበሽታ መከላከልና በፈውስ ህክምና ላይ ለተሰማሩ የጤና ባለሞያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጠ፡፡

    የዓለም ጤና ድርጅት/WHO ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ከድሬዳዋ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ለስድስት ተከታታይ ቀናት በሶስት ዙር በበሽታ መከላከልና በፈውስ ህክምና ላይ ለተሰማሩ ለመንግስትና ለግል የጤና ባለሞያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ስልጠናው በቅርቡ ወደ ጤና ተቋማት የወረዱትን ከኮቪድ-19 ወይም ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር የተያያዙ ተግባራት ሙሉ በሙሉ በጤና ተቋማት መተግበር የሚያስችል አቅም የሚፈጥር ነው፡፡
    በስልጠናው ፈጣን ምላሽ ሰጪ ግብረ-ኃይል ተግባርና ኃላፊነት፣ የመረጃ አያያዝ፣ አመዘጋገብ፣ ትንተና እና አጠቃቀም፣ የኮቪድ-19 በሽታ ስርጭት እና ችግሩ የሚከሰትባቸውን አካባቢዎች መለየት፣ እንዴት ጥቆማዎችን መለየትና ማረጋገጥ እንደሚቻል፣ በድንገተኛ ወረርሽኝ ወቅት ናሙና አሰባሰብ፣ አያያዝ፣ የጎዞ ሁኔታ እና ውጤቱን ማሳወቅ ላይ ባለሞያዎቹ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መደረጉን በዓለም ጤና ድርጅት/WHO የድሬዳዋ ቅርንጫፍ የኮቪድ_ 19 አስተባባሪ ዶ/ር ህይወት ታፈሰ ተናግረዋል፡፡
    ዶ/ር ህይወት አያይዘውም ድርጅቱ ከዚህ በፊትም ለጤና ባለሞያዎች የተለያዩ አቅም መገንቢያ ስልጠናዎችን፣ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝና ለሌሎች በሽታዎች አገልግሎት የሚውሉ መድሃኒቶችንና የህክምና መስጫ ቁሳቁሶችን እንዲሁም የማማከርና ከአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ጋር በመሆን የመከታተል ሥራን ሲሰራ መቆየቱንና በቀጣይም ከቢሮው ጋር ይህንኑ ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
    ምንጭ ድሬደዋ ጤና ቢሮ