የድሬ ደዋ አስተዳደር ዳያስፖራ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት በመስተዳደሩ በማህበራዊ አገልግሎት ላይ ከሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በተካሄደዉ ምክክር ዳያስፖራውን በማህበረሰብ የልማት ስራዎች ይበልጥ ለማሳተፍ በቅንጅትና በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለፀ፡፡
የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የድሬ ደዋ አስተዳደር የትምህርት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ወ/ሮ ሙሉካ መሀመድ እንደገለፁት በህብረተሰቡ የልማት ፍላጎት ላይ ያሉ ክፍተቶች እና ችግሮችን በሚገባ በመለየት የዳያስፖራውን ማህበረሰብ አቅምና ክህሎት በማሰባሰብ ህዝቡን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች ባለመሰራታቸዉ ድሬ ደዋ በዳያስፖራ መልማት ያለባትን ያህል አለመልማቷን ይህን ለመቅረፍ ባለድርሻ አካላት ተናበው እና ተቀናጅተዉ መስራት እንዳለባቸዉ ጠቁመዋል፡፡
የድሬ ደዋ አስተዳደር ዳያስፖራ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አክሊለ ታጠቅ በበኩላቸዉ በተለያዩ የውጭ ሀገራት ትውልደ ኢትዮጵያውያ ዳያስፖራዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን የልማት ስራዎች ላይ ከፍተኛ አስተዋፆ በማድረግ ላይ መሆናቸዉንና በተለይ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፣ ገበታ ለሃገር ፕሮጀክት በአጠቃላይ በ2013 በጀት አመት በግማሽ አመቱ 22.6 ሚሊየን ለገበታ ለሃገር የሚሆን ሀብት በውጭ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን መሰብሰቡን አብራርተዋል ፡፡
ባለፉት አምስት አመታት በአጠቃላይ በ5 አመት ውስጥ (ከ2008-2012 ዓ.ም) 15,260,453 ዶላር ( ከ550 ሚሊየን ብር በላይ) በውጭ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለመሰብሰብ ፣ በ2013 በጀት አመት በግማሽ አመቱ 90 ሚሊየን የተሰበሰበ ሲሆን በድሬ ደዋ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው ከ1998-2012 ዓ.ም 580 ዳያስፖራዎች ወደ ድሬደዋ የመጡ ሲሆን 234 የሚሆኑ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ካወጡ 78ቱ ወደ ስራ ገብተዋል 2276 ዜጎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የስራ እድል መፈጠሩን እና 2.2 ቢሊዮን ብር ኢንቨስት እንደተደረገ ገልፀዋል፡፡
የምክክር መድረኩ ላይ በአስተዳደሩ የተለያዩ የገጠር ቀበሌዎች የሚገኙ ከመሰረታዊ ከመማር ማስተማር መስፈርት በታች በሆነ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ት/ት ቤቶችን የሚያሳይ ፁሁፍ ቀርቦ በተሳታፊዎች ሰፊ ዉይይት ተካሄደበት ሲሆን የማህበራዊ አገልግሎት ፍላጎት በማሳባሰብና የተቀረጹ ፕሮጀክቶች በመቅረፅ ዳያስፖራው ለራሱ ቀጥተኛ ትርፍ ከሚያስገኝለት ስራዎች በተጨማሪ ማህበረሰባዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ለመገናኘት ተስማምተዉ ተለያይተዋል፡፡


