በየትምህርት ቤቱ የንባብ ማእከላትን ለማደራጀት በሚያስችል መልኩ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ ።

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብት መጽሐፍት ኤጀንሲ፣ ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲና ድሬዳዋ ባህልና ቱሪዝም ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የንባብ ሣምንት በድሬዳዋ አስተዳደር በይፋ ተጀመረ ፡፡
    ተማሪዎችና ወጣቶችን ማእከል በማድረግ ቀደምት የነበረውን የንባብ ባህልን በማጎልበትና በማሳደግ የተሟላና ጥሩ ስነ-ምግባር ያለው ጠያቂና ምክንያታዊ የሆነ ትውልድ መፍጠር እንዲሁም አዳዲስ ሀሳቦችን መፍጠር የሚችልና በምክንያት የሚያምን ትውልድን ለመፍጠር ታልሞ “መጽሀፍት ለእውቀት ገበታ መዛግብት ለዘመን ትውስታ” በሚል መሪ ቃል በትናንትናው እለት በለገሀር አዳባባይ የንባብ ሳምንት ተጀምሯል ።
    በለገሀር አደባባይም በተጀመረው የንባብ ሳምንት ላይ የመፅሀፍት ሽያጭ ኤግዚቢሽን የተካሄደ ሲሆን በዝግጅቱ ላይም በርካታ የመፅሀፍት ነጋዴዎች መፅሀፍትን ለአንባቢያን በቅናሸ አቅረበዋል ። በዛሬው እለት ደግሞ በምክር ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ በተዘጋጀው መድረክም በተለይም በድሬዳዋ አስተዳደር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የንባብ ክበባትን ማደራጀት አስፈላጊ በመሆኑ ምክንያት ይህንንም ማደራጀት በሚቻልበት አግባብ ዙሪያ በየትምህርት ቤቶቹ ያሉ መምህራንና ርዕሰ መምህራን እንዲሁም ተማሪዎች እንዲገኙ በማድረግ መድረኩ ተካሂዷል ።
    በተለይም በከተማችን ድሬዳዋ የሚገኙና መፅሀፍትን ድጋፍ ለሚሹ ወጣት ማእከላት እንዲሁም ትምህርት ቤቶች የመፅሀፍት ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ሀገራችን ላይ የሚገኙ ደራሲያንን ወደ ከተማችን ድሬዳዋ በማስመጣትና በተለይም የህፃናትን የማንበብ ክህሎትን ማሳደግ የሚቻልበትን ሂደት ለመፍጠር ያለመ መድረክ መዘጋጀቱን የድሬዳዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ሙራድ በደዌ ተናግረው በቀጣይም በየትምህርት ቤቱ የንባብ ማእከላትን ለማደራጀት በሚያስችል መልኩ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ሙራድ በደዌ ተናግረዋል ።
    የንባብ ሳምንት አካል የሆኑ ፕሮግራሞች በቀጣይም የሚካሄዱ ሲሆን ዛሬ ምሽትም ከአዲስ አበባ የሚመጡ ደራሲያንና የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች እንዲሁም በከተማዋ ላይ የሚገኙ የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች የሚሳተፉበት የኪነ-ጥበብ ምሽት ከመኖሩም በዘለለ በነገው እለት የህዝብ ላይብረሪዎችን ታሳቢ ያደረጉ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች እንደሚቀርቡም ታውቋል፡፡