አቶ አደም ፋራህ እና አቶ ኦርዲን በድሪ ትናንት በድሬዳዋ ከተማ አሸዋ ገበያ ማዕከል ላይ በእሳት አደጋ የደረሰውን ጉዳት ተመለከቱ

በምክትል ጠቅላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ እና የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ኦርዲን በድሪ ትናንት በድሬዳዋ ከተማ አሸዋ ገበያ ማዕከል ላይ በእሳት አደጋ የደረሰውን ጉዳት ተመልክተዋል።

አቶ አደም ፋራህ በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በዘላቂነት መልሶ ማቋቋም ይገባል ብለዋል።

በጉብኝቱ ወቅት ክቡር አቶ አደም ፋራህ በዚህ አደጋ ከፍተኛ ሀዘን እንደተሰማቸው የገለፁ ሲሆን የእሳት አደጋው በቁጥጥር ስር እንዲውል ርብርብ ላደረጉ አካላትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ለዚህም በድሬዳዋ አስተዳደር የተጀመረውን የመልሶ ማቋቋም ስራ ሁሉም አካል እንዲደግፍ ጠይቀዋል።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው፥ የእሳት አደጋው ከግለሰቦች ባሻገር በሐገር ኢኮኖሚ ላይ የራሱን አሉታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያሳርፍ ገልፀው፤ በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች መልሶ ማቋቋም የሁሉም ሐላፊነት ነው ብለዋል።

አስተዳደረሩ በአደጋው የተጎዱ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም እያደረገው ያለውን ጥረት የክልሉ መንግሥት እንደሚደግፍም አስታውቀዋል።

ልዑክ ቡድኑ የድሬዳዋ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስም የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ፣ የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ይሱፍ እንዲሁም የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦድሪን በድሪን ጨምሮ የአስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ አመራሮች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *