አጠቃላይ የጉዳት መጠን መለየትና በቀጣይ የመልሶ ማቋቋም ዝርዝር ተግባራትን ለማመላከት የተዘጋጀው መሪ እቅድ በክቡር ከንቲባው የሚመራ አስራ ሁለት አባላት ያሉት አብይ ኮሚቴና በስሩ አራት ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማደራጀት መሪ እቅዱን መነሻ አድርገው በአስቸኳይ ዝርዝር ተግባራትን አቅደው ወደ ስራ እንዲገቡ የሚያስችል ሲሆን ፤ ተጎጂዎችን ማረጋጋት ፣ የጉዳት ልየታና መልሶ ለማቋቋም ንዑስ ኮሚቴው የንብረት ጉዳትን በአይነት ፣ በብዛትና በገንዘብ ተመን መለየት እንደዚሁም ጊዚያዊ የገበያ ስፍራ እንዲመቻች ያደርጋል ተብሏል፡፡
የአብይ ኮሚቴውን አቅጣጫ ተከትሎ የቴክኒክ ኮሚቴው ወደ ስራ የገባ ሲሆን የንዑሳን ኮሚቴዎችን ዝርዝር ተግባራት በየሶስ ቀናቱ የሚያቀርቡት ሪፖርት መሰረት አድርጎ ግብረመልስ እየተሰጠ በአሰቸኳይ ጊዜያዊና ዘላቂ መፍሔዎች ላይ እንደ ሚሰራም ተገልጿል፡፡
መሪ እቅዱ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን እና ዝርዝር የድርጊት መርሃ ግብሮችን ያካተተ ሲሆን በቀረበው እቅድ ላይም የአስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና አመራሮች በሰፊው ተወያይተውበታል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጁሃር የእሳት አደጋው ያደረሰው ውድመት ከፍተኛ እና አስከፊ መሆኑን ገልጸው በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የአስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ያለማንም ጠሪ በስፍራው ላይ በመገኘት የተነሳው እሳት ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት እና እሳቱን ለመከላከል የሚደረገውን ርብርብ በቅንጅት እንዲከናወን ያደረጉት ጥረት የሚያስመሰግን ነው ብለዋል ፡፡
ከንቲባው አክለውም ይህ አስከፊ አደጋ የድሬዳዋን ህዝብ የጸና እርስበርስ የመተሳሰብና የመደጋገፍ ጠንካራ እሴት በተግባር ተገልጦ የታየበትና ሊመሰገን የሚገባው መሆኑን ጠቅሰው በተለይም የፀጥታ ኃይሎች የሚያገለግሉትን ህዝብ ከህይወታቸው አስቀድመው እሳቱን ለመቆጣጠር ያደረጉት ርብርብ ፣ እሳቱ በቁጥጥር ስር ከዋለም በኃላ ከቀን እስከ ለሊት የአካባቢውን ሰላም በመስጠበቅ ሂደት ላይ ያለንበት ተግባር ሊያስመሰግናቸው ይገባል ብለዋል፡፡
መሰል አደጋዎች ቢከሰቱ የከፋ ጉዳት ሳያስከትሉ ለመቆጣተር የሚያችሉ የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች ከወዲሁ በፍጥነት ሊከናወኑ እንደሚገባ ያሳሰቡት ከንቲባ ከድር ጁሀር በሌሎች የገበያ ማእከላትና የገበያ ስፍራች ድንገተኛ የእሳት አደጋ ማጥፊያዎች በሁሉም የንግድ ቤቶች ውስጥ እንዲደረጉ አስገዳጅ መመሪያ ወጥቶ ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸው ፣ እንደ አስተዳደርም ለድንገተኛ የእሳት አደጋ አገልግሎት የሚውሉ የውሃ መስመሮች ዝርጋታም እንደሚከናወን ገልጸዋል ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ክቡር ከንቲባው የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎችን አስመልክቶ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ ስልጠናዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተዘጋጅተው ለንግዱ ማህበረሰብ ሊሰጡ እንደሚገባ አሳስበዋል ፡፡
የተነሳው የእሳት አደጋ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ የአካባቢውን የንግድ ማህበረሰብ ተወካዮች በመሰብሰብ የማረጋጋትና ንብረት የወደመባቸውን ወገኖች መልሶ ለማቋቋም እና ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሔዎችን በጋራ በማፈላለግ አስተዳደሩ ከጎናቸው እንደማይለይ በመግለጽ ለዚሁ ተግባር ንዑሳን ኮሚቴዎችን የማደራጀት ስራ መሰራቱን የገለጹት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ ፣ የመልሶ ማቋቋም ስራው በአለማቀፍ የአደጋ ስጋት አመራር ስታንዳርድ እና በቅርብ አመታት መሰል አደጋዎች የደረሰባቸውን አጎራባች ክልሎች ልምድና ተሞክሮ በማቀናጀት በጥብቅ ዲሲፕሊን የምንመራው ይሆናል ብለዋ ፡፡
በተከሰተው የእሳት አደጋ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ ንብረቶቻቸው የወደመባቸው ነጋዴዎች መኖራቸውን ያነሱት የብጽግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሒም ይሱፍ አስቸኳይ የእለት እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን በፍጥነት በመለየት ቅድሚያ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ አስታውሰው ፤ የአደጋውን መንስኤ ለማጣራት ከሚከለለው አካባቢ ውጪ ያለውን በጊዜ አጽድቶ ወደ ስራ የሚገቡበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል ብለዋል ፡፡
የድሬዳራዋ ጠቅላይ ፖሊስ መምሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ በበኩላቸው በሰብአዊነት የማገልገል ፖሊሳዊ መርሑን ከራሱ ይልቅ ለህዝቡ ህይወትና ደህንነት በመስጠት የድሬዳዋ ፖሊስ የእሳት አደጋ መከላከል ዲቪዥን እና ሁሉም አባላት ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ሙያዊ ኃላፊነትና ግዴታቸውን በአኩሪ ሁኔታ መፈጸማቸውን ጠቅሰው ፤ በተለይም ከሁሉም በላይ ደግሞ ማታ አለኝ ብሎ የቆጠረውን ሀብትና ንብረቱን ማለዳ ላይ እሳት የነጠቀው ማህበረሰብ በዛ ከባድና አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በስፍራው ከተገኙት የአስተዳደሩ ከንቲባና አመራሮቻቸው ጋር የነበረው ቀና ትብብርና ቅንጅት የመሪና የተመሪ ሳይሆን ፍጹም ቤተሰባዊ ፍቅርና አንድነት የተስተዋለበት ነበር ሲሉ አድንቀዋል ፡፡
በእሳት አደጋው የደረሰው ከፍተኛ የንብረት ውድመት አሳዛኝ እንደሆነ ጠቅሰው ከፍተኛ አመራሩ የጸጥታ ኃይሎችና ህብረተሱ እሳቱን ለመቆጣጠር ያደረጉት ርብርብ የሚያስመሰግን እንደሆነ በመግለጽ የንግዱ ማህበረሰብ ሰርቶ ትርፋማ መሆን ሲችል ነው የምናቅዳቸውን የልማት ስራዎች ማሳካት የምንችለው ያሉት የድሬዳዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱሰላም መሐመድ በእሳት አደጋው ንብረቶቻቸው የወደሙባቸውን የንግዱን ማህበረሰብ አባላት በጊዜያዊነትና በዘላቂነት ለማቋቋም ከሚሰሩ ስራዎች ጎን ለጎን የግብር እፎይታ ፣ ውዝፍ እዳ ያለባቸው ካሉም ስረዛና ቅነሳንም ታሳቢ አድርገን እንሰራለን ብለዋል ፡፡
በአሸዋ የገበያ ስፍራ የተነሳው የእሳት አደጋ ዜና ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ የጎረቤት ሀገር ጅቡቲን ጨምሮ የአጎራባችና ክልሎችና መስተዳድሮች የተሰማቸውን ሀዘን በመግለጽ በመልሶ ማቋቋም ጥረታችንም ወቅት ከጎናችን እንደሚቆሙ እጠገለጹልን ይገኛሉ ያሉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጁሃር ለመልሶ ማቋቋም ሀብት የማፈላለግ ስራዎችም በተጠናና በተቀናጀ አግባብ ይከናወናሉ ብለዋል ፡፡
በመጨረሻም ከንቲባ ከድር ጁሃር በእሳት አደጋው ንብረቶቻቸው የወደመባቸውን ወገኖቻቸውን ከማረጋጋት ከተቻለም አቅም በፈቀደ መጠን በሃሳብና በገንዘብ ከመደገፍ ይልቅ የእሳቱ መነሻ ምክንያት ገና በውል ተለይቶ ባልታወቀበት ለእኩይ ዓላማቸው ትርፍ ፍለጋ መሰረተ ቢስ አሉባልታ በማናፈስ ውዥንብር ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላት ከዚህ ኢ ሞራላዊ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበው ፣ አስተዳደሩ ተጎጂዎችን ለማቋቋም በሚደርገው ጥረት በሀገር ውስጥና በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ከጎናችን እንድትቆሙ ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል::


