ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ እንዳሉት ያለ አግባብ በግለሰቦች እጅ የገባውን ገንዘብ ማስመለስ አስፈላጊ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በፊት ያለ አግባብ በግለሰቦች እጅ የተያዘ ገንዘብ ለማስመለስ የሚያስችል ሕግ እንዳልነበር ጠቅሰው፤ አሁን ግን ሕጉ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት እየተሠራበት ነው ብለዋል፡፡
በተደረገው ጥናት መጠኑ ብዙ የሆነ ገንዘብ በስማቸው መቀመጡን እንኳን በማያውቁ ግለሰቦች ስም መቀመጡ ተደርሶበት ሕጉ እንዲወጣ መደረጉን አንስተዋል፡፡
አዋጁ ንፁሃንን ለመንካት ሳይሆን ሌቦችን ለመቅጣት ያለመ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ጤነኛ የገንዘብ ዝውውር እንዲኖር እና ኢኮኖሚያችን እንዲረጋጋ አዋጁ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
አላግባብ ገንዘብ የሰበሰቡ ሰዎች በገንዘባቸው ማሕበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ሀሰተኛ መረጃዎችን እንደሚያሰራጩ ጠቅሰው፣ ሰዎች በነዚህ መረጃዎች ከመደናገር መሬት ላይ ያለውን እውነታ መረዳት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
የተደራጀ መንግሥታዊ ሌብነት አለመኖሩን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ማንኛውም የመንግሥት አካል በሌብነት ውስጥ መገኘቱትን ማስረጃ የሚያቀርብ ካለ እርምጃ ለመውሰድ አናመነታም ነው ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግሥታዊ ሌብነት ቢኖር ኖሮ አሁን እየተሠሩ ያሉ ፕሮጀክቶችን መሥራት አይቻልም ነበር ብለዋል፡፡


