የኛ ቁጠባ እና ብድር ሀላፊነቱ የተወሰነ የህብረት ስራ ማህበር 20 መኪናዎችን ለማህበሩ አባላት በዛሬው እለት አስረክበ

የኛ ቁጠባ እና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ የህብረት ስራ ማህበር በድሬዳዋ አስተዳደር ላይ በቁጠባ እና ብድር ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙ ማህበራት መካከል አንዱ ሲሆን ማህበሩ የነዋሪውን ህብረተሰብ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ። በዛሬው እለትም ከኤላውቶ ኢንጂነሪንግ የገዛቸውን 20 መኪናዎች ለማህበሩ አባላት አስረክቧል ።

በመኪና ርክክብ ስነ-ስርአቱ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጁሀር የኛ ቁጠባ እና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ የህብረት ስራ ማህበር ነዋሪው ህብረተሰብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን ላይ በመስራቱ አመስግነው በዛሬው እለት መኪናውን የተረከቡ የማህበሩ አባላትም የአስተዳደሩን ገፅታ በሚያጎላ መልኩ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸውም ነው ክቡር ከንቲባው በእለቱ ያስታወቁት ።

የኛ ቁጠባ እና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ የህብረት ስራ ማህበር ከተቋቋመ አንድ አመት ቢሆነውም ከአንድ ሺህ አንድ መቶ በላይ አባላትን ማፍራት መቻሉን የኛ ቁጠባ እና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ የህብረት ስራ ማህበር ዋና ሊቀመንበር አቶ ዳንኤል ታደሰ ተናግረው ለአባላቱም ከ 75 ሚልዮን ብር በላይ ብድር መሰጠቱንም ነው አቶ ዳንኤል ታደሰ የተናገሩት ።

ዘመናዊ ታክሲዎችን በመግዛት እና በከተማዋ ላይ ለማሰማራት ታልሞ ማህበራቸው መመስረቱን የየሎው ስታር ታክሲ ማህበር ሀላፊ የሆኑት አቶ ሙሉቀን ፍቅሩ ተናግረው በዛሬው እለት የተረከቧቸው መኪናዎች በድሬዳዋ አየር መንገድ እንዲሁም በከተማዋ ላይ የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠታቸው ጎን ለጎን የከተማዋን ስም ለመገንባት እንደሚሰሩም ነው አቶ ሙሉቀን ያስታወቁት ።

በእለቱም ከትናንት በስቲያ በድሬዳዋ አስተዳደር ልዩ ስሙ አሸዋ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባለው የገበያ ስፍራ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ ንብረታቸው ለወደመባቸው አካላት የሚውል የኛ ቁጠባ እና ብድር ሀላፊነቱ የተወሰነ የህብረት ስራ ማህበር የ 100 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍም አበርክቷል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *