በኦሮምኛ ሙዚቃ እድገት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጾ ያበረከተው የአፍረን ቀሎ የሙዚቃ ቡድን 62ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በድሬዳዋ ከተማ ተከብሯል ፡፡

በኦሮምኛ ሙዚቃ እድገት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጾ ያበረከተው የአፍረን ቀሎ የሙዚቃ ቡድን 62ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በርካታ ታዳሚዎች በተገኙበት ዛሬ በድሬዳዋ ከተማ ተከብሯል ፡፡

ቋንቋና ባህልን ለማሳደግ መሰባሰብ እጅግ ፈታኝ በነበረበት ዘመን ተሰባስበው የኦሮምኛ ተወዳጅ የሙዚቃ ስራዎቻቸውን በሬዲዮ ለህዝቡ ጆሮ እንዲደርስ እና ባለ ተሰጥኦ ወጣቶችን በማሰባሰብ በርካታ ስመጥር የሙዚቃ ባለሞያዎች እንደፈጠሩ ምቹ መደላድል የፈጠሩት የአፈድረን ቀሎ የሙዚቃ ቡድን አባላት 62ኛ የምስረታ በዓል ሲከበር የቡድኑ መስራች የሆኑት አርቲስት ኡስማኤል ሙመድ አደም እና ሌሎች ከጀርን ፣ ከካናዳ ፣ ከአውስትራሊያና ከአሜሪካ ሀገር ተሰባስበው በስነስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል ፡፡

ለኦሮሞ ቋንቋና ባህል እድገት እንደዚሁም ኪነጥበብ እባዜን እውን በማድረግ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የአፍረን ቀሎ የሙዚቃ ቡድን 62ኛ ዓመት ምስረታ መከበሩ በቀደሙት ጉምቱ የኪነጥበብ አባቶች ዳና የሚጓዙ ወጣት ከያኒያንን ለማፍራት ትልቅ መደላድል ነው ያሉት የድሬዳዋ አስዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከዲር ጁሃር በስነስዓቱ ላይ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች መጥተው የታደሙ የቀድሞ የቡድኑን መስራቾችና አባላት አመስግነዋል ፡፡

ኪነጥበብ በየትኛውም የህዝብ ትግል ውስጥ ያላትን ጠንካራ አቅም በመጠቀም የህዝባችንን ብሶት ለመግለጽና የፖለቲካዊ ንቃት ለማዳበር አፍረን ቀሎ የሙዚቃ ቡድንን መስርተን በመሰባሰብ ኪነጥበብን ለትግላችን በመሳሪያነት ተጠቅመናል በማለት የቡድኑ መስራች አርቲስት ኡስማኤል ሙመድ አደም ከዛሬ 62 ዓመት በፊት የነበረውን ሁኔታ አስታውሰው ፤ ቡድኑ ሙዚቃ መስራት ብቻ ሳይሆን ለኦሮምኛ ቋንቋ እድገትም ምርምርና ጥናት ያደርጉ እነደነበር እና ዛሬም ላይ በዘልማድ የሚባሉና መሰረታዊ የፍቺ ዝንፈት ያለባቸውን ቃላት በመጥቀስ በወቅቱ የተሰሩ ስራዎችን ለአብነት ለስነስርዓቱ ታዳሚያን አብራርተዋል ፡፡

በወቅቱ በቡድኑ ስብስብ ውስጥ የነበሩና ዛሬም ድረስ ዘመናትን ተሻግረው የሚደመጡ የኦሮምኛ የሙዚቃ ስራዎችን ግጥምና ዜማ የደረሱ አባላት አስተዋጾና አበርክቶ በመድረኩ ላይ የተወሳ ሲሆን በመድረኩ ለኦሮሞ ህዝብ ሁለተናዊ እድገትና ለውጥ ኪነጥበብን ብርቱ መሳሪያው አድርጎ ታግሎና አታግሎ የተሰዋው አቡበከር ሙሳ ስራዎች ተነስተዋል፡፡

የአፍረን ቀሎ 62ኛ ዓመት ምስረታ በዓል ሲከበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ የቡድኑ አባላት በስራዎቻቸው በኦሮሞ ህዝብና የኪነጥበብ አፍቃሪያን ልቦና ውስጥ ህያዋን ሆነው የሚታወሱና ታሪክ የሚዘክራቸው መሆናቸውን ጠቅሰው ተተኪ ወጣቶች ይህን ፈለግ ተከትለው ባህልና ቋንቋቸውን እንዲያሰድጉ ሙዚቃውን በማዘመን ወደ ዓለማቀፍ ተደማጭነትና ተቀባይነት ለማሻገር መትጋት እንደሚጠበቅባቸውና አስተዳደሩም አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግላቸው ተናግረዋል ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *