የድሬዳዋ አስተዳደር አካባቢ ፣ የደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን እና የድሬደዋ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በጋራ የተሰናዳ የውሃ ብክለትንና ብክነትን ለመቆጣጠር በሚቻልባቸው የአሰራር ሂደቶች ዙሪያ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የተለያዩ አካላት ጋር ምክክር ተካሂዷል።
በመድረኩ የድሬደዋ አስተዳደር የአካባቢ የደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ አብዶ መሀመድ በውሃ ሃብት ክምችት መመናመን ሊያስከትሉ የሚችሉ በርካታ ጉዳቶች በማወቅም ሆነ በቸልተኝነት አየተፈጠሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በመሆኑም የውሃ ብክለትን ለመከለል እና ለመቆጣጠር ብሎም የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ የውሃ ሃብት ክምችት መልሶ ማገገም እንዲችል ህብረተሰቡም ሆነ በዘርፉ የሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ስራ አስኪሃጁ አሳስበዋለወ።
የድሬደዋ የዉሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ መሀመድ ሙሴ በበኩላቸው፥ ድሬዳዋ ላይ የሚስተዋለን የውሃ ብክለት ለመቆጣጠር የተለያዩ ስራዎችን እየሰሩ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በውሃ ክምችት ላይ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ በሆኑ ክስተቶች የሚደርስ ጉዳት እንዲሁም ባልተገራ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም የተነሳ በሚከሰት ብክነት እና ብክለት የንፁህ መጠጥ ውሃ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውንም አቶ መሀመድ ሙሴ ጠቁመዋል ።
ከፍሳሽ አወጋገድ እና የብክለት መንስኤ በሆኑት አደገኛ የቁሻሻ ዙሪያና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ፁሁፍ የቀረበ ሲሆን በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል።
በቴክኖሎጂ የተደገፈ የብክለት መከላከያ ዘዴ መከተል የቁሻሻ አወጋገድ ባህላችን መሻሻል እንዳለበት እና የቁሻሻ ምንጭ የሆኑት አገልግሎት ሰጪዎች እና ማህበረሰቡ ብሎም የጤና ተቋማት በጉዳዩ ላይ ትኩረት ተሰጥተው መስራት እንዳለባቸው በምክክር መድረኩ ተጠቁሟል።


