የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ምክኒያት በማድረግ የገበያ ዋጋን ያለአግባብ በሚጨምሩ ህገወጥ ነጋዴዎች ላይ እየተወሰዱ የሚገኙ ህጋዊ እርምጃዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ

የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ እና ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ቢሮ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ምክኒያት በማድረግ የገበያ ዋጋን ያለአግባብ በሚጨምሩ እና የኮትሮባንድ ንግድን በሚያካሂዱ ነጋዴዎች ላይ እየተወሰዱ የሚገኙ ህጋዊ እርምጃዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና ንግድ እና ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ ክቡር አቶ ሀርቢ ቡህ መንግስት የኢትዮጵያን የምጣኔ ሀብት እድገት በተሟላ መልኩ ለማስቀጠልም አሁን ላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ሙሉ ትግበራ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪና የአቅርቦት ችግር እንዲፈጠር በሚያደርጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ እርምጃ በመውሰድ የተረጋጋ የኑሮ ሁኔታ እንዲፈጠር እየተሰራ መሆኑን ገለጹ።

የንግዱ ማህበረሰብም የኑሮ ዉድነቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲታቀብም ጥሪ ቀርቧል።

ህብረተሰቡም ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ አላስፈላጊ ጥቅም ለማግኘት የሚያንቀሳቅሱ ነጋዴዎችን ጥቆማ በመስጠት ከመንግስት ጎን እንዲቆምም ነው ምክትል ከንቲባ ክቡር አቶ ሀርቢ ቡህ ያሳሰቡት።

የአስተዳደሩ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ቢሮ የንግድ ጽ/ቤት ከጸጥታው መዋቅር ጋር በመሆን ህገወጥ የዋጋ ጭማሪ እና የአቅርቦት ችግር እንዳያጋጥም በቅንጅት በተሰራው ሥራ በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦችና የታሸጉ የንግድ ተቋማት መኖራቸውን የንግድ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ አብዲ ሙክታር ተናግረዋል።

ምርት በመደበቅና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ 81 የንግድ ድርጅቶች ላይ የማሸግና በህግ ቁጥጥር ሥር ዉለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *