የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የ2016 ዓ.ም የስራ አፈፃፀም እና የልካም አስተዳደር ሪፖርት ግምገማ መድረክ እንዲሁም የ2017 ዓ.ም ዕቅድ ላይ የውይይት መድረክ በዛሬው ዕለት አካሂዷል፡፡
በውይይት መድረኩ የ2016 በጀት አመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርትና የ2017 ዓ.ም እቅድ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ሪፖርት የተቋሙ ሰራተኞችን ጨምሮ የሴክተር ተቋማትና የወረዳዎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በመድረኩ የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ብሩክ ፈለቀ የኮሚዩኒኬሽን ስራ በጋራ የሚሰራ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን በቀጣይም ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጠናከር ስራዎች እንደሚሰሩ አመላክተዋል፡፡
አቶ ብሩክ አያይዘውም በተለይም በ2017 ዓ.ም የተለየዩ የሶሻል ሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም ለማህበረሰቡ ፈጣንና ወቅታዊ መረጃዎችን ተደራሽ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በአስተዳደሩ የሚከናወኑ ትልልቅ ሁነቶችን በቀጥታ ስርጭት ሽፋን በሶስት ቋንቋዎች ማሰራጨቱ የመረጃ ተደራሽነቱ እንዲሰፋ ማስቻሉንና ማህበረሰቡም ካለበት ቦታ በመሆን ታማኝና ትኩስ መረጃዎችን ቦታ ሳይገድበው ማግኘት መቻሉ ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ከመድረኩ ተነስቷል፡፡
በመድረኩ ሀሳብ የሰጡ ተሳታፊዎች ከእናት መስሪያ ቤት ጋር በመደጋገፍ ስራዎችን መስራት ውጤታማ እንደሚያደርግ ገልፀው ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር ይገባል የሚሉና መሰል ተያያዥ ሀሳቦችን አንስተዋል፡፡


