የድሬደዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ አቡበከር አዶሽ በዛሬው ዕለት የ201 7 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በትምህርት ቤቶች ቅኝት በማድረግ ጭምር በይፋ ያስጀመሩ ሲሆን በቢሯቸውም መግለጫ ሠጥተዋል።
አቶ አቡበከር የ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን መከፈት አስመልክቶ በሠጡት መግለጫ በተቀመጠው መስፈርት መሠረት ምዝገባዎች በአብዛኛው በመጠናቀቃቸው የ2017 ዓ.ም ትምህርት ዛሬ መስከረም 7 በይፋ መጀመሩን ገልጸዉ በትምህርት ሴክተር የተሰማሩ የዘርፉ አመራሮችና ባለሞያዎች ትልቁ ሀላፊነት የተማረ ዜጋ ማፍራት እንደመሆኑ ለዚህ ሁሉም የድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በ2016ዓም በትምህርት ሴክተሩ የነበረው ክፍተት በተለይ በገጠሩ ማህበረሰብ በኩል የትምህርትን ፋይዳ አለመረዳት፣የተማሪዎች በሰዓቱ ትምህርት ገበታ ላይ አለመገኘት፣ የመምህራን ከስራ ገበታ መቅረትና የሴት ተማሪዎች አናሳ ተሳትፎ ይጠቀሳሉ ያሉት ምክትል ሀላፊው በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በተለይ ርዕሰ መምህራንና የበላይ አካሎች በክትትልና በቁጥጥሩ በኩል ትልቅ ሀላፊነታዊ ግዴታን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።
አቶ አቡበከር አዶሽ አክለውም አሁን ላይ የትምህርት ዘርፉ ከትምህርት ቢሮ አና ከባለድርሻ አካል ብቻ ሳይሆን ከሁሉም የማህበረሰብ ክፍል እገዛ እንደሚፈልግ ጠቅሰው ለዚህም የድሬዳዋ ትምህርት ቢሮ የመማሪያ ቁሳቁስና ኮምፒውተሮችን ጨምሮ የተለያዩ የመማር ማስተማሩን ሂደት የሚያግዙ ድጋፎች ከተለያዩ አካላት እያገኘ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
እጅ አጠር ተማሪ በትምህርት ሴክተሩ እንዳይኖር ከሚደረገው ርብርብ በተጨማሪ በትምህርት ለትውልድ ፕሮግራም ከእያንዳንዱ ተቋም ኮምፒውተር የማሠባሠቡ ሂደት መጀመሩንም የትምህርት ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ አቡበከር አዶሽ ተናግረዋል።
በመጨረሻም ለ2017 ዓ.ም ትምህርት ዘመን ለትምህርት ሴክተሩ በተደረገው እገዛ ከ41 ሚሊየን ብር በላይ የመማሪያ ቁሳቁስና ሌሎች ድጋፎች መደረጋቸውንና ድጋፉ በትክክል የሚያስፈልጋቸውን ተማሪዎች ልየታ እየተከናወነ መሆኑንም ነው ምክትል ሀላፊው በመግለጫቸው የገለፁት።


