የድሬዳዋ አስተዳደር ከተማ ስራ አስኪያጅ ፅ/ቤት በታሪፍ ማሻሻያ ባወጣው ረቂቅ መመሪያ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እካሄደ

የድሬዳዋ አስተዳደር ከተማ ስራ አስኪያጅ ፅ/ቤት የመኝታ አገልግሎት ግብር አሰባሰብ አመዘጋገብና የሪፖርት አቀራረብ መመሪያ ቁጥር 1703/2017 ላይ በዛሬው እለት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል::

በውይይት መድረኩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከተማ ስራ አስኪያጅ ፅ/ቤት ኃላፊ ኢንጂነር ጀማል ኢብራሂም በዛሬው መድረክ በዋነኝነት የመኝታ ግብር ለማሰባሰብ በወጣው ረቂቅ መመሪያ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየትና ግብአት በማሰባሰብ የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ መመሪያውን ወደ ስራ ለማስገባት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል::

በድሬዳዋ አስተዳደር ከተማ ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት የመሰረተ ልማትና የማዘጋጃ ገቢ ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ ኢብሳ አሜ በበኩላቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ የማዘጋጃ ገቢዎች የሚሰበሰቡበት የተለያዩ 49 ኮዶች መኖራቸውን አንስተው እንደ ድሬዳዋ አስተዳደር ግን ከ 11 ኮዶች ብቻ እንደሚሰበሰብ ተናግረዋል::

በዚህም አሁን ላይ በአስተዳደሩ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ስራ ያልገቡ ኮዶችን ወደ ስራ ለማስገባት ስራዎችን እየተሰሩ መሆኑን አቶ ኢብሳ አብራርተው በዛሬው መድረክም የመኝታ አገልግሎት መመሪያን ወደ ስራ ለማስገባት ከባለድርሻ አካላት ጋር ግብአት የማሰባሰቢያ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል::

መመሪያው በዚሁ በ 2017 ዓ.ም ላይም ወደስራ እንደሚገባ አቶ ኢብሳ አመላክተዋል::

በቀጣይም በዚሁ በ 2017 ዓ.ም የጫኝና አውራጅ እንዲሁም የተረፈ ምርት ኮዶችን ወደ ስራ ለማስገባት ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እየተሰሩ መሆኑን አቶ ኢብሳ ጠቁመዋል::

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *