#DGC ህዳር 8/2017፧
ተቋሙ እየሰጣቸው ባሉ የብድርና ቁጠባ አገልግሎቶችም ወጣቶችና ሴቶችን በይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ መጠነ-ሰፊ ስራዎች እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል።
የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በድሬዳዋ አስተዳደር እያከናወናቸው ያሉትን አገልግሎቶችን ተደራሽነት በማስፋት በምስራቁ የአገራችን ክፍል በሐረር ከተማም ቅርንጫፎችን በመክፈት እየሰራ ይገኛል።
ተቋሙ በሐረር የሚገኙ ምስጉን ደንበኞቹን ዕውቅና ለመሥጠትና ከደንበኞቹ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ኮንፍረንስ በሐረር ከተማ አካሂዷል።
በኮንፍረንሱ ላይ የተገኙት የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተሾመ አበበ ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ደንበኞቹ ሃብቶቹ፣ ደንበኞቹ የህልውናው መሠረት መሆናቸውን በፅኑ የሚያምን ተቋም መሆኑን ጠቅሰው ደንበኛ ንጉስም ክቡርም እንደሆነም በቅጡ ይረዳል ብለዋል፡፡ ለዚህም ነው ሁሌም ለደንበኞች ዕርካታ ከፍተኛ ትኩረት በመሥጠት እየሰራ የሚገኘው ያሉት ዋና ስራአስፈፃሚው በሐረር ከተማ ከውድ ደንበኞቹ ጋር የሚያቀራርበውን፣ለቀጣይ የሰመረ የደንበኞች ግንኙነቱም መሠረት የሚጥለውን የደንበኞች ኮንፍረንስ ያዘጋጀው ለዚህ ነው በማለት ተናግረዋል፡፡
ይህ የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ የሐረር ደንበኞች ኮንፍረንስ በቀጣይ ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ከደንበኞቹ ጋር ለሚኖረው መስተጋብር የማዕዘን ድንጋይ መሆኑን የገለፁት አቶ ተሾመ ኮንፍረንሱ ከደንበኞቹ ለቀጣይ ስራዎቹ ግብዓት የሚያገኝበት፣ የደንበኞቹን ፍላጎት በይበልጥ ለማርካት ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት እንዲሰራ ብርቱ ኃይል የሚሰንቅበትን ምቹ መደላድል የሚፈጥርለት መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈፃሚው ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ የወጣቶችና ሴቶችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ለማሳደግ መጠነ-ሰፊ ስራው እየተሰራ መሆኑን አውስተው ይህንንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
በኮንፍረንሱ ስለ ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ታሪካዊ ዳራና አሁናዊ ሁኔታን ገላጭ የሆነ የመወያያ ፅሁፍ በተቋሙ ዋና ስራአስፈፃሚ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በውይይቱ በኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ የቁጠባ ባህላቸው እንዲያድግ መሠረት እንደሆናቸውና አካል ጉዳተኞችንም ተደራሽ በማድረግ ትርጉም ያላቸው ሥራዎችን እየሰራ እንደሆነና ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተመላክቷል። ከወለድ ነፃ አገልግሎት ያገኘነውም በድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ነው ሲሉም የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች ሃሳባቸውን አካፍለዋል። በቀጣይም ተቋሙን ወደ ላቀ ደረጃ ያደርሰዋል ያሏቸውንም ገንቢ ሃሳቦች ሰጥተዋል። የውይይቱ አወያዮችም ከመድረኩ ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ ሰጥተውባቸዋል።
በኮንፍረንሱ በድሬ ማይክሮ ፋይናንስ በሐረር በሚገኙት የሐረር አራተኛና የሐረር ካናል ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ቅርንጫፎች ደንበኞች የሆኑ ምስጉን የብድርና ቁጠባ ደንበኞች እንዲሁም ከተቋሙ ጋር በጋራ እየሰሩ ያሉ አጋር አካላት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።ሲል ዘገባውን ያደረሰን ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ነው።


