በድሬዳዋ አስተዳደር የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማሳደግ እና ውጤታማ ለማድረግ ስራዎችን በርብርብና በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የአስተዳደሩ ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር ገለፁ::

#DGC ህዳር 19/2017

በዛሬው ዕለት የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማበረታታት እንዲሁም “የኢትዮጲያ ታምርት ንቅናቄን” ለመደገፍ የጋራ የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ።

በዚህም በመድረኩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር በኢንደስትሪው ዘርፍ የሚሰሩ ስራዎችን በቅንጅት መስራት ውጤታማ እንደሚያደርግ ተናግረው፤ “የኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄም በድሬዳዋ አስተዳደር ተስፋ ሰጪ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ አመላክተዋል።

በአስተዳደሩ ከዚህ ቀደም የተዘጉ 31 ኢንደስትሪዎች አሁን ላይ የተከፈቱ መሆናቸውን የተናገሩት ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሃር ይህ ለሀገራችን እድገት ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳለው ገልፀው፤ በቀጣይም ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ከግብ ለማድረስ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ክቡር ከንቲባው ጠቁመው ባለድርሻ አካላትም እያበረከቱት ላለው አስተዋፆም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊና አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ አብዲ ሙክታር በበኩላቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ በድሬዳዋ አስተዳደር ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልፀው ቅንጅታዊ አሰራር መኖሩ አንዳንድ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

አቶ አብዲ ሙክታር አያይዘውም የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍን ለመደገፍም በዛሬው ዕለት ከ 26 ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የስምምነት ሰነድ መፈራረማቸውን ገልፀው ይህም በቀጣይ በ2017 ዓ.ም የሚሰሩ ስራዎችን ሁሉም ባለድርሻ አካላት አውቀው የራሳቸውን ሀላፊነት እንዲወጡ ለማስቻል የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል።

በኤደን ሳሙኤል

ፎቶ:- ሙሉዓለም ደሴ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *