“ሀይማኖቶች ለሰላምና ለአብሮነት” በሚል መሪ ቃል በድሬዳዋ አስተዳደር እንደ ሀገር የመጀመሪያ የሆነ የሰላም ኮንፍረንስ ታህሳስ 12/2017 ዓ.ም በድሬዳዋ ኢንተርናሽናል እስታዲየም ሊካሄድ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ በዛሬው እለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።
የኮንፍረንሱ ዋነኛ አላማም የድሬዳዋ ህዝብ በፍቅር፣ በአብሮነትና በአንድነት ሰላሙን አስጠብቆ እየኖረ በመሆኑ ለመላው የድሬዳዋ ህዝብና ለከተማ አስተዳደሩ እንዲሁም ለሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምስጋናና እውቅና ለመስጠት፤ እንዲሁም ይህንን የሰላም እሴት ለሌሎችም የሀገራችን አካባቢዎች በተሞክሮነት ለማሳየት መሆኑ ታውቋል።
ድሬዳዋ ከፍቅር ከተማነቷ በተጨማሪም በዚህ ኮንፍረንስ የሰላም ተምሳሌት ካባንም እንደምትደርብ ተገልጿል።
በመርሀ-ግብሩ የኢትዮጲያ የሀይማኖት ተቋማት የበላይ ጠባቂ አባቶች፣ ከፌደራል የሚመጡ የክብር እንግዶች፣ የሁሉም ክልል የሀይማኖት ተቋማት ተወካይና የሰላም ቢሮ ተጠሪዎች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች የሚገኙ ይሆናል።
በዚህም ፕሮግራሙ ከጠዋቱ 12:30 ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን የዱአ፣ የምስጋናና የቡራኬ መርሀ ግብር ሲኖር፤ ለድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር የሰላም አንባሳደርነት ማእረግ እንደሚሰጥም ተጠቁሟል።
በመድረኩ የሰላም ዋንጫ ከድሬዳዋ ተነስቶ ወደሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች እንደሚዛወር የተገለፀ ሲሆን፤ የድሬዳዋ አስተዳደር ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤም ሁሉም የድሬዳዋ ህዝብ ፕሮግራሙን እንዲታደም ጥሪ በማቅረብ፤ በተለመደውና በሚታወቀው የድሬዎች የእንግዳ አቀባበል ባህል እንግዶችን መቀበል ይገባናል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በኤደን ሳሙኤል
ፎቶ:- ሰላም አበበ


