#DGC ህዳር 28/2017
የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን በቢዮ አዋሌ ክላስተር አዳዳ ገጠር ቀበሌ ላይ መምህራን ፣ ተማሪዎችንና ማህበረሰቡን ያሳተፈ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ድህረ እንክብካቤ ስራዎችን አከናወኑ።
የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የደን ልማት ቡድን መሪ አቶ ማሙሽ ዘውዱ በመርሃግብሩ ማስጀመሪያ ወቅት እንደገለፁት ችግኞችን ከተከሉ በኋላ በመኮትኮት ፣ ውሃ በማጠጣትና ከበሽታ በማከም ቢያንስ ለሶስት አመታት ክትትል ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል።
አክለውም በአዳዳ ገጠር ቀበሌ የተተከሉት ችግኞች ጥሩ አቋም ላይ እንደሚገኙ አስረድተው ይህም በህብረተሰቡ እና አመራሩ ጠንካራ የክትትል ስር እንደመጣ ጠቁመዋል።
ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በተሰራው የኤስ ኤስ ዳም አማካኝነት ዉሃን በመያዝ የተተከሉትን ችግኞች ለማጠጣት እየተጠቀሙ እንደሚገኝ ያስረዱት የአዳዳ ገጠር ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ መሀመድ ዩሱፍ ከአዳዳ ገጠር ቁ.1 እና ቁ.2 አንደኛ እና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች ፣ መምህራንና ማህበረሰቡ በንቅናቄ እንደተሳተፉበት ገልፀዋል።
በመረሃግብሩ ወቅት ያነጋገርናቸው መምህራን እንደገለፁት አርብቶ እና አርሶ አደር ማህበረሰብ የሚበዛበትን የገጠር ቀበሌውን ከበረሃማነት ለመታደግ ተማሪዎችን ያሳተፈ በየአስራ አምስት ቀናት የሚከናወን የእክብካቤ ስራ እንደሚካሄድ ገልፀዋል።
በትምህርት ቤቶች ላይም የአካባቢ ጥበቃ ክበባትን በማቋቋም የዛፎችን ጠቀሜታ ፣ የደን ጭፍጨፋ ጉዳቶችን እንዲያውቁና ውሃ የማጠጣት ባህልን እንዲያዳብሩ ግንዛቤ በመስጠት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በድሬዳዋ አስተዳደር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃግብር እስካሁን ከ2.4 ሚሊየን በላይ የደን ፣ የውበት እና የጥምር ደን ችግኞችን በሁሉም የከተማ እና ገጠር ክፍሎች መተከላቸው ይታወሳል።


