ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ያደረጉት ስምምነት ከሁለቱ ሀገራት ባሻገር ለሌሎች የቀጠናው ሀገራት እና ለቀጠናው ሰላም ትልቅ እፎይታ ነው ሲሉ የአፍሪካ ጉዳዮች ተማራማሪ አቶ ሙሉጌታ ከተማ ይፍሩ ገለፁ፡፡
ተመራማሪው ከኢቢሲ ዶትስትሪም ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የስምምነት ዜናው ግጭቱን ለራሳቸው ተጠቃሚነት ለማዋል ያሰቡ ሀገራትን እና በቀጠናው የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖችን ከዓላማቸው የሚያደናቅፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ስምምነቱ ውጤታማ እንዲሆንም ያሉ ችግሮችን እየነቀሱ በመፍታት፤ ሀገራቱ መተማመን ላይ የተመሰረት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲኖራቸው መሰራት እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡
የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ በቀጠናው የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖችን ጥቃት የመከላከል እና የቀጠናው መረጋጋገት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም ውጥረቱ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን “ምን ይፈጠር ይሆን?” ስጋት ያረገበ እና ወደ ቀድሞ ወንድማማችነት የመለሰ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
በቀጣይ የኢትዮጵያ ተጠቃሚነት እንዴት ሶማሊያን ሊጠቅም እንደሚችል ማሳያ የሆኑ ስራዎችን ማቀድ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡
አክለውም መንግስት ከሶማሊላንድ ጋር የፈፀመው ስምምነት ግልፀኝነት እና ተግባራዊነት ላይ የሶማሊያን ሉዓላዊነት ያልተጋፋ መሆኑን ሊያስመሰክር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሙሃመድ የአንካራው ስምምነት በተፈረመበት ወቅት፤ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ለችግር ተጋላጭ በመሆኑ በትብብር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም የኢትዮጵያ ወታደሮች ለሶማሊያ ሰላም የከፈሉት መስዕዋትነት አይዘነጋም በማለት፤ በቀጣይም ሶማሊያ የኢትዮጵያ ጥሩ ወዳጅ ሆና ትቀጥላለች ማለታቸው ይታወሳል፡፡
EBC


