የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከጅቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ እና ሌሎች የሀገሪቱ የስራ ሃላፊዎች ጋር በወደብ አጠቃቀም እንዲሁም በሌሎች የሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ተናገሩ።
በጅቡቲ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ሚኒስትሩ ከጅቡቲ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፥ የጉብኝቱ ዓላማ በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ለማድረግ ነው።
ኢትዮጵያና ጅቡቲ በጣም ልዩ እና ጠንካራ ትብብር እንዳላቸውም ገልጸዋል።
ከጅቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ እና ከውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ጋር በሁለትዮሽ እና በቀጣናዊ የፖለቲካና የደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።
በንግድ ጉዳዮች፣ በወደብ አጠቃቀም እና በወቅታዊ ቀጣናዊ ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያም መምከራቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በአጠቃላይ ከባለስልጣናቱ ጋር ገንቢ እና ፍሬያማ ውይይት እንዳደረጉ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያና ጅቡቲ በባቡር፣ በወደብና መሰረተ ልማት መስኮች ዘመናትን የተሻገረ ታሪካዊ ወዳጅነት ያላቸው አገራት ናቸው።
የኢትዮጵያ እና ጅቡቲ መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እ.አ.አ በ1984 እንደተጀመረ መረጃዎች ያመለክታሉ።


