የኮንስትራክሽን ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ

የድሬዳዋ አስተዳደር የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ መልዕክት

ቢሯችን የተቋቋመው የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የአስፈፀሚና ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አካላትን እንደገና ለማቋቋምና ተግባርና ሃላፊነታቸውን ለመወሰን ባወጣው አዋጅ ቁጥር 68/2014 ነው፡፡ ስያሜም “የድሬዳዋ አስተዳደር የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ” በሚል የተቀየረ ሲሆን የቢሮው ሥልጣንና ሃላፊነትም በተጠቀሰው አዋጅ በአንቀጽ 55 ሥር ተደንግጓል፡፡ በዚህ አንቀጽ ሥር የተቀመጡትንና የተደነገጉትን የተቋሙን ሥልጣንና ሃለፊነት መነሻ በማድረግም የከተማ ልማት፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪና የቤቶች የልማት ዘርፎችን ተግባራት ለማከናወን፣ ለማስተባበርና ለመምራት የሚያስችል ዕቅድ ተዘጋጅቶና በቢሮው ማኔጅመንት ተገምግሞ ወደ ሥራ ከተገባ ወራት ተቆጥረዋል፡፡

ተቋማችን በአዋጅ ተሰጠውን ሥልጣንና ተግባር ለመወጣትም ሆነ የዘርፎቹን አገራዊና አስተዳደራዊ የልማት አስተዋጽኦ ለማጠናከር፣ የአስተዳደሩን ነዋሪዎች የዘርፎቹን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግና ሌሎች የልማት ዘርፎች የሚፈልገጉትን የመሰረተ ልማት አቅርቦት ለማሻሻል የታቀዱ የልማት ተግባራትም ከ2015 ዓ/ም በጀት ዓመት መግቢያ አንስቶ በተካሄደ እንቅስቃሴ በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በተከናወኑ ተግባራትና በተፈፀሙ ዕቅዶችም አበራታች ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ አበራታች ውጤቶች የተመዘገቡትም ትኩረት ተሰጥተው በመተግበራቸው ብቻ ሣይሆን በአስተዳደር ደረጃ የተቀመጠውን አቅጣጫ በመከተል የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች በመሰራታቸው ነው፡፡

የሪፎርም ሥራዎችን ለማጠናቀቅና መደበኛ ሥራዎቻችንን በቅደም ተከተል አስቀምጠን በትኩረት በመሥራት የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠልም እያንዳንዱ ተጠሪ ተቋማትና የሥራ ክፍሎች የ60 ቀን ዕቅድ አዘጋጅተው እንዲተገብሩ ተደርጓል፡፡ ይህም ዕቅድ በላቀ ደረጃ እንዲፈፀምና የአፈፃፀም ችግሮችን ለይቶ ፈጣን ምላሽ ለመስጠትም በየሳምንቱ የሚገመገምበትና አቅጣጫ የሚቀመጥበት አሰራር ተዘርጋቶ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ ይህን ማድረግ ያስፈለገውም ቢሯችን የተቋቋመባቸውን የከተማ፣ የኮንስትራክሽና የቤቶች የልማት ዘርፉች ለአስተዳደራችንም ሆነ ለአገራችን የኢኮኖሚ ዕደገት፣ የብልጽግና ጉዞ ስኬታማነት፣ ለድህነት ቅነሳና ለዜጎች ኑሮ መሻሻል የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ስለሚታወቅ ነው፡፡

የአገራችንም ሆነ የአስተዳራችንን የኢኮኖሚ ዕደገት ለማፋጠንም ሆነ የመሰረተ ልማት አቅርቦትን ለማሳደግ የሚቻለው ዘመናዊና ተወዳደሪ ከተማ በማልማት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ቀደም ብሎ ቢሯችን የተቋቋመው ሶስት የልማት ዘርፎችን ሥራዎች ለመሥራት፣ ለመምራትና መላስተባበር መሆኑ ቢገለጽም ሁሉም ከተማ ልማት በሚለው ዘርፍ ሊጠቃለሉ ይችልሉ፡፡ ምክንያቱም የአንድ ከተማ ልማት የሚፋጠነውም ሆነ የተወዳደሪነት አቅም የሚገነባው በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪና በቤቶች ልማት ውጤቶች መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ኮንስትራክሽን በከተማ ልማት ዘርፍ ውስጥ የሚገኘው ነው የሚያሰኘውም ሁሉም ውጤቶቹ ለኢኮናሚና ማህበራዊ ልማት፣ ለአምራችና ለአገልግሎት ሰጭ ዘርፎች እንደግብዓት የሚያገለግሉ የመሰረተ ልማት ውጤቶችን የሚያቀርቡ በመሆናቸው ነው፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ እየሰራ ያለውና በቀጣይም ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራው የድሬዳዋ ከተማን የተወዳደሪነት አቅም ለማጎልበት የሚያስችሉ ውጤቶችን ለማስመዝገብ ነው የሚለውን አቅጣጫ በሚገባ ማጤና ለተግባራዊነቱ መረባረብ የምያስገኘው ፋይዳም በቀላሉ የሚገመት አለመሆኑን መረዳትም ቅድሚያ የሚሰጠው ነው፡፡ ምክንያቱም የህብረተሰቡን ፍልጎት በሚያሟሉና የልማት ጥየቄዎችን በሚመልሱ ጥራት ባላቸው የኮንስትራክሽንና የመሰረተ ልማት አቅርቦት የድሬዳዋን ዘመናዊነትና ተወዳደሪነት ማረጋገጥ ከሚያስገኘው ጠቀሜታ በተጨማሪም ጥልቅ ትርጉም ያለው መሆኑ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል፡፡ የድሬዳዋን ዘመናዊነትና ተወዳደሪነት ማረጋገጥ ልዩ ትርጉም የሚሰጠውም ከከተማዋ ወቅታዊና ቀጣይ ሁኔታዎች ጋር በማያያዝ ለመረዳት ሲሞከር ነው፡፡ ለዚህም ማስረጃ ከሚሆኑ ዕድሎችና መልካም አጋጣሚዎች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰውም የከተማችን ለጂቡቲ የወደብ ከተማ ያላት ቅርበትና የደረቅ ወደብ አገልግሎት የምትሰጥ የምስራቅ ኢትዮጵያ የንግድ ከተማና የነፃ የንግድ ከተማ በመሆን መመረጧ ነው፡፡ የእነዚህና የመሳሰሉት ዕድሎች ተጠቃሚ ለመሆን የሚቻለውም መላው ህብረተሰብና ባለድርሻ አካላት ቢሯችን ያዘጋጀውን ዕቅድ ለመተግበር በሚደረገው እንቅስቃሴ የበኩላቸውን ድርሻና ሃላፊነት መወጣት ሲችሉ ነው፡፡ እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍልና ባለድርሻ አካላትም ሃላፊነታቸውን መወጣት የሚችሉት የጎላና ውጤታማ ተሳትፎ ሲያደርጉ መሆንን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳር የከተማልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የድሬዳዋን የብልጽግና ማዕከልነት የሚያረጋግጡና ሁሉንም ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን በማከናወን አበራታች ውጤቶችን እያስመዘገቡ መሆኑን የሚመለከት ሐሳብ ለማቅረብ የተሞከረው ግን ተስፋ ሰጭና ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉ ለመጠቆም እንጂ ቢሮው በሚያደርገው ጥረት ብቻ የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል ለማለት ተፈልጎ አይደለም፡፡ የሶስቱን የልማት ዘርፎች በተለይም የከተማዋን ልማት ለማፋጠንና ከመሰረት ልማት አቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚቻለው የመላውን ህብረተሰብና የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ በማሳደግ መሆኑን ካለመረዳት አይደለም፡፡ በተለይም ከመሰረተ ልማትና ከኮንስትራክሽን ውጤቶች አቅርቦትና ጥራት ጋር የተያያዙ ችግሮችን መቅረፍ የሚቻለው በህብረተሰቡና በባለድርሻ አካላት የነቃ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

የመሰረተ ልማትና የኮንስትራክሽን ውጤቶች አቅርቦትና ጥራት ዋነኛ ችግሮች ናቸው ከሚባሉት መካከል ዋናዎቹም የግንባታዎች የጥራት መጓደል፣ የመጓተት (የመዘግየት) ፣ የመቋረጥና የተጋነነ በጀት ጭማሪ ናቸው፡፡ የእነዚህ ችግሮች መንስኤዎች ናቸው ከሚባሉትም መካከል ጥቂቶቹ የግንባታ ባለቤቶች ለሚያስገነቡት ህንፃ ወይም ሌላ የግንባታ አይነት የሚሰጡት ትኩረት አናሳ መሆን፣ የግንባታ ባለቤቶች ወይም የተወካዮች ፣ በግንባታው ሥራ ላይ ወሳኝ ሚና ያላቸው ሶስት አካላት የሚያደርጉት ያልተገባ የጥቅም ግንኙነት፣ የሥራ ተቋራጮች፣ የአማካሪዎችና የባለሙያዎች የማስፈፀም አቅም ዝቅተኛ መሆን፣ የግንባታ ባለቤቶች የዲዛይን ፍላጎት ወጥ አለመሆንና የዲዛይን ለውጥ እንዲደረግላቸው መጠየቅ፣ ወዘተ ናቸው፡፡

እነዚህንና ሌሎቹን ተግዳሮቶች መቅረፍ የሚቻለው በህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ ነው የሚባለውም ያለምክንያት አይደለም፡፡ ማንኛውም የግንባታ ሥራ የሚሰራበት ጊዜና ቦታ ስላለው ከህብረተሰቡ እይታ ውጭ ሊሆን አይችልም፡፡ ሁሉም ነገር በህብረተሰቡ እይታ ውስጥ መሆኑ ብቻ ግን ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል መፍትሄ ሊያስገኝ አይችልም፡፡ ከህብረተሰቡ እይታ ጋር በተያያዘ ችግሮቹን ማስወገድ የሚቻለው ህብረተሰቡ ለመንግሰትም ሆነ ለግል ግንባታዎች ያለው አመለካከት ሲስተካከል ወይም ነገ የምገለገልባቸው እኔ ነኝ፡፡ በመንግስትና በህዝብ ሀብት የሚገነባ ማንኛው የግንባታ ውጤት የእኔና የቀጣዩ ትውልድ ሀብት ነው የሚል አስተሳሰብ በማዳበር በማንኛውም የግንባታ ሥራ ተሳታፊዎች የሚመለከታቸውን ያልተገቡ የጥቅም ግንኙነቶችን ሲያጋልጥና የግንባታውን ሂደት በመከታተል የተመለከተውን ችግር አግባብ ላለው አካል በማቅረብ ነው፡፡ ህብረተሰቡ በባለቤትነትና በያገባኛል ስሜት የመከታተል ልምድ ካዳበረም ሶስቱ የግንባታ ሥራ ወሳኝ ተዋናኞች የሚፈጥሩትን ያልተገባ ግንኙነት የሚከላከል ውጤት ሊያስመዘብግ ይችላል፡፡

በሥራ ተቋራጮች፣ በአማካሪዎችና በግንባታ ዘርፍ በተሰማሩ ባለሙያዎች ላይ የሚስተዋለው የማስፈፀም አቅም አናሳነት ወይም የዕውቀትና የክህሎት ክፍተት ችግር የሚቀረፈውም በእነሱ ተሳትፎና የመለወጥ ፍላጎት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ምክንያቱም ቢሯችን ከሚሰጣቸው አገልግሎቶችን ከሚያደርጋቸው ድጋፎች ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው የአቅም ግንባታ አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ በመሆኑም የዕውቀት፣ የክህሎትና የአቅም ችግር ያለባቸው ሥራ ተቋራጮች፣ አማካሪዎችና በግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ቢሮው በሚያዘጋጀው የአቅም ግንባታ ሥልጠና ላይ በመሳተፍ የማስፈፀም አቅማቸውን ማጎልብትና ጥራት ያላቸውን የኮንስትራክሽን ውጤቶች ለማቅረብ ይችላሉ፡፡

ከግንባታ ባለቤቶች በኩል የሚስተዋለው የዲዛይን ፍላጎት ወጥ ያለመሆንና የዲዛይን መቀያየር ችግር የሚቀረፈው ደግሞ ከዲዛይን ዝግጅት በፊት በሚከናወኑ ተግባራትና ጥናቶች ነው፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም የግንባታ ባለቤት ዲዛይን እንዲዘጋጅለት ጥያቄ ከማቅረቡ በፊት የፍላጎት ትንተና፣ የግንባታውን የቀጣይ አገልግሎትና አካባቢያዊ ተጽዕኖ ወይም ለፈጠሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን መረዳት፣ የግናባታውን ቦታ ለግንባታ ሥራ ነፃ ማድረግና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ይኖርበታል፡፡

የአገርን ልማት የሚያፋጥነውና የግብዓት አቅርቦት ችግሮችን የሚቀርፈው አዳዲስ ግብዓቶችን መግዛትና መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት ብቻ አይደለም፡፡ የተዘረጉ የመሰረተ ልማቶችንና የግንባታ ውጤቶችን በቁጠባ መጠቀምና መንከባከብም ሌላው ለዕድገት የሚያበቃ ልምድ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ መላው ህብረተሰብና ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሰጡትና ተሳትፎ ሊያደርጉበት የሚገባው ሌላው ጉዳይም የኮንስትራክሽንና የመሰረተ ልማት ውጤቶችን በአግባቡ የመጠቀምና የመንከባከብ ባህል ማዳበር ነው፡፡ ይህም የመንግስት ህንፃዎችን አጠቃቀም የሚመለከት ነው፡፡ ቢሯችን አገልግሎት ከሚሰጥባቸውና የከተማውን ልማት ለማፋጠን አቅዶ ከሚንቀሳቀስባቸው ዘርፎች መካከል አንዱም የመንግስት ህንፃዎችና ቤቶችን የሚመለከት ነው፡፡ በዚህም ዘርፍ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች የሚስተካከሉት በህብረተሰቡ፣ በባለድሻ አካላትና በተጠቃሚዎች ተሳትፎ ነው፡፡ ስለሆነም ከመንግስት ህንፃዎችና ቤቶች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ ለምናደርገው ጥረት ውጤታማነት የሁሉም ዜጋ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ መረዳትና ለተግባራዊነቱም ሃላፊነትን መወጣት የግድ ይላል፡፡

በከተማ ልማት፣ በኮንስትራክሽንና በመሰረተ ልማት ዘርፍ ላይ የሚያጋጥሙትንና የተጠቀሱትን ተግዳሮቶች ለመከላከል የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማረጋገጥ ከተቻለም ከተማችንን ለማልማትና ነዋሪዎችንም በወቅቱ የተፈጠሩ መልካም ዕድሎችና አጋጣሚዎች ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል አፍ ሞልቶ መናገር ይቻላል፡፡ በመሆኑም ህብረተሰቡም ሆነ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ተሳትፎ ካደረጉና ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ከሞከሩ የከተማችንን ዘመናዊነትና ተወዳዳሪነት በማረጋገጥ የሶስቱም የልማት ዘርፎች ተጠቃሚ እንደምንሆን መረዳት ያስፍልጋል፡፡ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥም ቢሯችን በሶስቱም የልማት ዘርፎች የሚሰጠውን አገልግሎት ውጤታማ የሚያደርግ ተሳትፎ ለማረጋገጥ በጋራ እንቀሳቀስ በማለት መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

ኢ/ር ጀማል ኢብራሂም ጎድ