ፍትህ ፀጥታና ህግ ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ መልእክት

የድሬዳዋ አስተዳደር ፍትህ ፀጥታና ህግ ጉዳዮች ቢሮ በአዋጅ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በአስተዳደሩ ጎልተው ይታዩ የነበሩትን በተለይም በፍትህ ስርዓቱ ላይ ይቀርቡ የነበሩ አቤቱታዎችን በመለየት የመብት ጥሰት ጉዳዮችን በመመርመርና በማጣራት የተገልጋዩን ህብረተሰብ ችግር በመፍታት፤ የወሰን እና የድንበር ግጭቶችን በመነጋገርና በመቻቻል መንፈስ በመቅረፍ፤ ሀገሪቱ ለጀመረችው የእድገት ጎዳና የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲያበረክት ቆይቷል፡፡ በዚህም አበረታች ውጤት ተገኝቶበታል፡፡ 
ቢሮው የህብረተሰቡ ንቃተ ህግ እንዲዳብር የህግ ጥናቶችን በማድረግ እና የህግ ረቂቆችን በማዘጋጀት መብትና ግዴታውን የሚያውቅ፣ ነገሮችን በህግ አግባብ ብቻ የሚፈታ ማህብረሰብ ለመፍጠር በርካታ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፡፡ 
ከዚህ በተጨማሪ በአስተዳደራችን ሰላም እና ፀጥታ ይበልጥ የተቀላጠፈ እንዲሆን ህዝቡም የሰላምና የፀጥታው፣ የፍትህና መልካም አስተዳደር ባለቤት ሆኖ ሂደቱን በመደገፍ ይበልጥ የተሳካ ለማድረግ ስራዎች ሁሉ በሰራዊት ቅኝት መከናወን እንዳለባቸው ታምኖ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ በዚህም መላውን የአሰርተዳደሩን ነዋሪ እስከ ብሎክ በመውረድ በ1 ለ5 አደራጅቶ እና አስተሳስሮ መጠነ ሰፊ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ 
ከዚህ ጎን ለጎን ሀገራችን የጀመረችውን ፈጣን እድገት ለማደናቀፍ የሚደረጉ እንደ ኪራይ ሰብሳቢነት ያሉ አመለካከቶችን በቁርጠኝነት በመታገል ልማታዊ እና ዲሞክራሲያዊ አመለካከቶች እንዲያብቡና የባለቤትነት ስሜት እንዲፈጠር፤ በሀይማኖት ሽፋን አፍራሽ ተልዕኮዎችን አንግበው የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን ከህብረተሰቡ በመነጠል እኩይ ተግባራቸውን ለማክሸፍና የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት በማስጠበቅ በኩል መላው የአስተዳደሩ ነዋሪ ከጎናችን ሊቆም ይገባል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከተማችን 6ተኛውን ሀገር አቀፍ የከተሞች ፎረም ከህዳር 6 እስከ ህዳር 13/2007ዓ.ም ለማክበር ሽርጉዷን ጨርሳ እንግዶቿን በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች፡፡ በመሆኑም የፍቅርና የመተሳሰብ ካባ የተላበሰው ህዝባችን በዓሉ በሰላም ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ በተለመደው የእንግዳ ተቀባይነት ባህሉ ከአስተዳደሩ ጎን እንዲቆም እጠይቃለሁ፡፡ 
በመጨረሻም መላው የአስተዳደሩ ነዋሪ ህገ-መንግስቱ የሰጠውን የመምረጥ መብት በመጠቀም ለግንቦት 2007ዓ.ም ሀገር አቀፍ ምርጫ ካርድ በመውሰድ በምርጫው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግና ምርጫው ሰላማዊና ፍትሃዊ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት እየጠየቅኩ መልዕክቴን እቋጫለሁ፡፡
አመሰግናለሁ!!