የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት ትራምፕ ከእስራኤል እና ከሱዳን መሪዎች ጋር በነበራቸው ቆይታ የሕዳሴ ግድብን አስመልክተው ፍጹም ተቀባይነት የሌለውን ሐሳብ ማራመዳቸውን ተከትሎ መግለጫ አውጥቷል።
ትራምፕ ኢትዮጵያ ግድቡን መገንባቷ አግባብ አለመሆኑን እና ግብፅም ግድቡን ልታፈርሰው እንደምትችል ሀገራቸውም የጀመረችውን እርዳታ የማቋረጡን እንደምትገፋበት ተናግረዋል።
ይህን አስመልክቶ መንግሥት በወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ በፈጣሪዋ ታምና በሕዝቧ አንድነት እና ጽናት የቆመች ሀገር መሆኗን ገልጿል።
ጥቂት ሰጥተው ብዙ ሊያዟት በሚሞክሩ ተማምና እንደማታውቅ እና እምነቷ ሕይወታቸውን ሰጥተው ሊታዘዟት በተዘጋጁ ልጆቿ ላይ እና የፈጠራት አምላኳ ላይ እንደሆነ ነው የገለጸው።
ልጆቿ በከፈሉት መሥዋዕትነት ዓለምን ጉድ ያሰኙ ታሪኮችን የሠራች ሀገር እንደሆነችም አስታውቋል።
እነዚህን አስደናቂ ታሪኮችን ስትሠራ አብረዋት ታሪክ የሠሩ ወዳጆች ነበሯት። የከዷት ወዳጆችም ነበሩ።
ይህ ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም።
ነገር ግን የዓለም ታሪክ ያረጋገጣቸው ሁለት ሐቆች አሉ። ኢትዮጵያን ነክቶ በሰላም የኖረ የለም የሚለው ቀዳሚው ነው።
ኢትዮጵያውያን በአንድነት ለአንድ ዓላማ ከቆሙ ድል ማድረጋቸው አይቀርም የሚለው ደግሞ ሁለተኛው።
የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ ግድብ ነው። ኢትዮጵያውያን፣ አሰቡት፤ ኢትዮጵያውያን ጀመሩት፤ ኢትዮጵያውያን ገነቡት፤ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ይጨርሱታል። አይቀሬ ነው።
የሚያዋጣን ኅብረት አንድነታችን ነው። ለእኛ ያለነው እኛ መሆናችንን ዐውቀን ስለ እኛ ጉዳይ እኛው ራሳችን ኢትዮጵያን አለንሽ እንበላት።
ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን ለኢትዮጵያ እንቁም። ከባዱ ፈተና ከውጭ የሚመጣው አይደለም። ከባዱ ፈተና ተለያይተን ችግሩን ከተጋፈጥነው ነው።
ማንም ገዝቶን አያውቅም። ወደፊትም ማንም አይገዛንም። ታሪክ የሠሩ እጆች ዛሬም አሉ።
ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ወዳጆቻቸውን ለማክበር እንጂ ጠላቶቻቸውን ለመታዘዝ ተንበርክከው አያውቁም። ዛሬም ወደፊትም አናደርገውም።
ክንዳችንን እናበርታ። ትከሻችንን እናስፋ። ልባችንንም እናጽና። ከውጭ እና ከውስጥ የተሠነዘረብንን ጥቃት ድል አድርገን መሻገር ብርቃችን እንዳልሆነ እናስመስክር።
በምንም እና በማንም ካሰብነው መንገድ እንቀርም። ያቀድነውን ከማሳካት የሚያግደን ምድራዊ ኃይል የለም።
አንድ ሆነን የምንይዘው ጋሻ ኃያላኑን ሁሉ ሲመክት የኖረ ነው። ዛሬም ያንን ጋሻ በአንድነት እናንሣ።
ሁላችንም፣ በየቦታችን፣ 24 ሰዓት፣ ለኢትዮጵያ እንቁም።
የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት


