በዚህም ለበርካታ ጊዜያት የህዝብ ጥያቄ የነበሩ በአሰሊሶ ክላስተር የአሰሊሶ ሁላሁሉ የ8.5 ኪ.ሎ ሜትር መንገድ እንዲሁም የገደንሰር የ6.5 ኪ.ሎ ሜትር የመንገድ ጥገና ስራዎች መፈታታቸውን በዛሬው ዕለት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የከተማ ልማት ኮንስትራክሽንና ማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በመስክ ተመልክተዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ ግንባታና ጥገና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ያሲን አህመድ በአሰሊሶ ክላስተር አሰሊሶ ሁላሁሉ የ8.5 ኪ.ሜ ጥገና ፕሮጀክት ከ 2 ወር በፊት የተጀመረ መሆኑን ገልፀው፤ አሁን ላይ የጥገና ስራው መጠናቀቁን ተናግረዋል።
አቶ ያሲን አያይዘውም በገደንሳር 6.5 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገና እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም መንገዱ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለማህበረሰቡ አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልፀዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የከተማ ልማት ኮንስትራክሽንና ማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ቤዛ ዳምጠው በበኩላቸው የገጠር መንገዶች ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱ በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ መሆኑን ገልፀው፤ ከዚህ ቀደም በአሰሊሶ ክላስተር አሰሊሶ ሁላሁሉ የ8.5 ኪ.ሜ ጥገና ፕሮጀክት ሳይሰራ በፊት መንገዱ አስቸጋሪና በተለይም ዝናብ በሚዘንብበት ጊዜ ጭቃ በመሆን ነዋሪዎችን የሚያማርር እንደነበረ ተናግረው አሁን ላይ ግን ጥገናው መሰራቱ ይህንን ችግር በመቅረፍ ነዋሪውን ማስደሰቱን ተናግረዋል።
በመንገዱ ሲገለገሉ ያነጋገርናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መንገዱ በመሰራቱ ከእንግልት መላቀቃቸውን ገልፀው አስተዳደሩን አመስግነዋል።
በኤደን ሳሙኤል
ፎቶ:- ሙሉዓለም ደሴ


