በድሬዳዋ አስተዳደር የተገነባው የድሬ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በዛሬው እለት በይፋ ተመርቋል ።
የድሬ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታ በአስተዳደር ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የመንግስት አገልግሎት እና አስተዳደር ሪፎርም ውጤታማ ለማድረግ የማይተካ ሚና የሚኖረው ከመሆኑም በላይ የተቋማት አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ የተደገፉ ፣ ቀልጣፋና ጥራት ያላቸው እንዲሆኑ ማድረግ የሚቻልበትን አቅም በመፍጥር ስማርት ድሬዳዋን እውን ለማድረግ እየተደረገ ያለውን ጥረት በእጅጉ የሚያጠናክር ምቹ አጋጣሚ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጁሀር ተናግረዋል ።
በኢ.ፌ.ድ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር አብይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነት በስፋት ተግባራዊ እየሆነ ያለውና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግርን በእጅጉ የሚፈታው የአንድ ማዕከል አገልግሎት በድሬዳዋ አስተዳደር ላይም ተግባራዊ በመሆኑ በእጅጉ መደሰታቸውን የኢ.ፌ.ድ.ሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር የሆኑት ክብርት እናትዓለም መለስ ገልፀው፤ የአንድ ማእከል አገልግሎቱ በከተማ አስተዳደሩ ላይ ተግባራዊ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፆ ላበረከቱም ምስጋባቸውን አቅርበዋል ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ሀገራዊ አቅጣጫ የሆነውን የመንግስት አገልግሎት እና አስተዳደር ሪፎርም በመተግበር የመንግስት ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ ፣ ጥራት ያለው ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እና ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን በዚህም የሪፎርም ትግበራው አንድ አካል የሆነውን እና የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ\ር አብይ አህመድ ኢኒሼቲቭ የሆነውን መሶብ ድሬ አንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱን የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የንግድ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም የመሶብ ድሬ አንድ ማዕከል አገልግሎት አስተባባሪ አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ክቡር አቶ ሀርቢ ቡህ ተናግረዋል ።


