የ2018 በጀት ዓመት የካፒታል ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የቃል-ኪዳን ሰነድ ፊርማ ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ

የካፒታል ፕሮጀክት የቃል -ኪዳን ሰነዱን የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር በተገኙበት 19 ተቋማት ተፈራርመዋል።

“በ2018 በጀት አመት በአስተዳደሩ ከተያዙ የካፒታል ፕሮጀክቶች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ የንፁህ የመጠጥ ውሀና የመስኖ ውሀ ፕሮጀክቶች እንዲሁም የጋራ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ትኩረት እንደሚደረግ ከንቲባ ከድር ጁሀር በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ ገልፀዋል።

በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ከአዲስ እና ነባር ፕሮጀክቶች መካከል በተለይ በገጠርና በከተማ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር የንፁህ የመጠጥ ውሀና የመስኖ ውሀ ፕሮጀክቶች ትኩረት እንደሚደረግባቸው የገለጹት ከንቲባ ከድር ጁሀር ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ጋር ተያይዞ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር በፍጥነት ወደ ስራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ከንቲባው በተጨማሪ የህብረተሰቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍም የመንገድ ዝርጋታን በተመለከተ ነባሮቹን ማጠናቀቅና አዳዲስ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ዝርጋታ ሥራዎች ሌላው ትኩረት የተደረገባቸው ፕሮጀክቶች መሆናቸውን አንስተው ነባሮቹም ሆኑ አዲስ የሚጀመሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው መስመር እንዲጓዙ ተቋማት በእኔነት ስሜት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

በካፒታል ፕሮጀክት ቃልኪዳን ሰነድ ፊርማ ስምምነቱ ሲካሄድ አጠር ያለ ማብራሪያ የሰጡት የአስተዳደሩ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ሙሉካ መሀመድ በበኩላቸው በ2017 የካፒታል ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በጥሩ መልኩ በውጤት ረገድ የሚለካ መሆኑን ገልጸው የ2018 ዓ.ም ደግሞ ነባር ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እና አዳዲሶቹን ደግሞ በተያዘላቸው ዕቅድ መሠረት ለማስኬድ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ለካፒታል ፕሮጀክቶች በ2018 ዓ.ም በአጠቃላይ 7.9 ቢሊየን ብር በጀት መያዙን የጠቀሱት ሀላፊዋ ከዚህ ውስጥም ሰባ በመቶው ለነባር ፕሮጀክቶች፥ ሀያ ዘጠኝ በመቶው ደግሞ ለአዲስ ፕሮጀክቶች መደልደሉን አስታውሰዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *