በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ መስከረም 16 ቀን የሚከበረው የደመራ በዓል በዛሬው ዕለት በድሬዳዋ በለገሀር አደባባይ በተለያዩ ሀይማኖታዊ ክዋኔዎች በድምቀት ተከብሯል፡፡
በበዓሉ ላይ የሀይማኖት አባቶች፣የድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፣ቀሳውስትና ዲያቆናት፣ምዕመናንና ከተለያዩ አለማት የመጡ ቱሪስቶች ተሳትፈዉበታል።
በበዓሉ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይና የከንቲባ ፅ/ቤት እና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊው አቶ ገበየሁ ጥላሁን በመገኘት ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላላፈዋል፡፡
የመስቀል ደመራ በዓል ከሀይማኖታዊ ትርጓሜው ባሻገር የነዋሪዉ ህዝብ ህብረብሄራዊ አንድነት አብሮነት ጎልቶ የሚታይበት ታላቅ በዓል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የመስቀል በዓል ሀገሪቱ በብዙ ፈተናዎች መሀል ገንብታ ያጠናቀቀችው የኢትዮጵያውያን አንድነት ተምሳሌት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ በተመረቀበት ማግስት እና የኢትዮጵያ ማንሰራራት የጀመረበት ወቅት መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገውም ነዉ የገለፁት።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዲዮስ አባል ብፁዕ አቡነ በርተለሜዎስ በበኩላቸው መስቀል ለሰውልጆች ሰላም ድህነት እንዲሁም የብርሀን ማብሰሪያ ነው ሲሉ ተናገረዋል፡፡
ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር ሀይማኖታዊ አስተምሮ በተከተለ መልኩ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።


