የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮና ተጠሪ ተቋማት የክረምት በጎ-ፈቃድ አገልግሎት አካል በሆነው የአቅመ ደካሞች የቤት እድሳት በተለያዩ ወረዳዎች የአረጋውያን ቤቶችን እያስገነቡ ይገኛሉ በዛሬው ዕለትም በወረዳ አራት ሁለት የአቅመ ደካማ ቤቶችን ግንባታ አስጀምረዋል።
በዚህም በመርሃ-ግብሩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲ ሙክታር ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በሰው ተኮር ተግባራት አቅመ ደካማ ወገኖችን የማገዝ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የተጀመሩ ቤቶችንም ከባለሀብቶች ጋር በመተባበር እንደሚገነቡ አቶ አብዲ ገልፀው፤ ቤቶቹም በአንድ ወር ግዜ ውስጥ ግንባታቸው ተጠናቆ ለባለቤቶች ርክክብ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
አቶ አብዲ አያይዘውም በከተማው የሚገኙ ባለሀብቶች በበጎ ተግባራት ላይ በመሰማራት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ በመሆኑ አመስግነው በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በቀጣይም ሰው ተኮር በሆኑ ተግባራት አቅመ ደካማ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን የማገዝ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ አብዲ ገልፀዋል።
በዛሬው ዕለት የቤት ግንባታው የተጀመረላቸው የወረዳ አራት ነዋሪ የሆኑት የ3 ልጆች እናት መሳይ ጌታቸው እና እናት ዘይነባ ኢድሪስ የሚኖሩበት ቤት የፈራረሰ፣ ዝናብ እና ፀሀይ የሚያስገባ መሆኑን ተናግረው አሁን ላይ ቤታቸው ሊገነባላቸው በመሆኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።
በዘንድሮ የክረምት የበጎ ፍቃድ ስራ እንደ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮና ተጠሪ ተቋማት 8 የአቅመ ደካማ ወገኖችን ቤት ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።


