በዛሬው ዕለት የድሬዳዋ አስተዳደር ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የ2017 ዓ.ም እቅድ ክንውን እና 2018 ዓ.ም መሪ እቅድ ላይ ከድሬዳዋ አስተዳደር የከተማ ወረዳዎች አመራሮች ጋር እንዲሁም ከከተማ አጎራባች ገጠር ቀበሌ አመራሮች ጋር ተወያይቷል።
የመልካ ቁጥር ሁለት የንፁህ መጠጥ ውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ላይ ከተደረገ የመስክ ምልከታ በማስቀጠል ሰፊ የመድረክ ውይይት የተደረገ ሲሆን የባለ ስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር መሀመድ ሙሴ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተቋሙ በመደበኛና በፕሮጀክት የተያዙ እቅዶችን ለመፈፀም ሲንቀሳቀስ መቆየቱን አብራርተዋል።
አስተዳደሩ ካለው ውስን በጀት ላይም ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማውጣት የመልካ ቁጥር ሁለት የንፁህ መጠጥ ውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት በራስ አቅም እንዲገነባ የተደረገ መሆኑን የገለፁት ስራ አስኪያጁ ፕሮጀክቱ 12 የውሀ ጉድጓዶች፣ 5 ሺህ ሜትር ኩብ መያዝ የሚችል ሪዘርቫየር (ቢርካ)፣ ከ58 ኪ. ሜ በላይ የመስመር ዝርጋታ ያካተተ ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑ ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ አሁን ላይ ከ40 ኪ.ሜ በላይ የመስመር ዝርጋታው የተጠናቀቀእንደሆነ እና አስፈላጊ ግብአቶች ግዢ መፈጸሙን ሀላፊው አንስተው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ የአስተዳደሩን የውሃ አቅርቦት በመጨመር ችግር ፈቺ እንደሆነም ተናግረዋል።
በዘርፉ በተለይም ከተደራሽነት ጋር ተያይዞ የውሀ መስመሮች በጨው የመደፈን፣ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ፣ ህገ ወጥ የውሃ አጠቃቀም፣ የመለዋወጫ እቃዎች ዋጋ መናር እና የበጀት እጥረት በበጀት አመቱ ተግዳሮት የነበሩ መሆናቸውንም ስራ ስኪያጁ አመላክተዋል።
2018 የመልካን ኘሮጀክት ማጠናቀቅ፣ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እና ገቢ አሰባሰብን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራም ኢንጂነር መሀመድ ሙሴ ተናግረዋል።
የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች ተቋሙ እየሰራው ያለዉ ስራ አበረታች መሆኑን በመጥቀስ፤ በቀጣይ ከአፋጣኝ ጥገና ጋር በተያያዘ፣ የሚቆፈሩ መንገዶችን በአግባቡ ከመመለስ፣ ሰራተኞች ተገቢውን መታወቂያ ከመያዝ አንፃር በትኩረት መሰራት እንደሚገባው አመላክተዋል።
በውይይቱ ማጠቃለያ ኢ/ር መሀመድ ሙሴ የወረዳ አመራሮች ህብረተሰቡን በማስተባበር ህገ-ወጥነትንና የስነ ምግባር ግድፈቶችን ለተቋሙ ማጋለጥ እንደሚገባ እንዲሁም አጥፊዎች ላይም ህግን የተከተለ አስተማሪ እርምጃ ለመውሰድ ተቋሚ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።


