የተፋሰስ ልማት ስራን በአግባቡ በመስራት ሁለንተናዊ ብልጽግናችንን እናረጋግጣለን ሲሉ የገንደ ገበሬ አርሶ አደሮች ተናገሩ::

    ገንደገበሬ በአሰሊሶ ክላስተር ስር ከሚገኙ 9 የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ቀበሌው በዋናነት በመስኖ ልማት ስራ የሚታወቅ ሲሆን በዚህም የቀበሌው አርሶ አደሮች የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በማምረት ለገበያ የሚያቀርቡ ከመሆኑም በላይ የድሬዳዋ መገለጫም ጭምር የሆኑት አምቦሾክ፣ ቲምር እና ሌሎችም ፍራፍሬዎች የሚመረቱበት ቀበሌ ነው፡፡
    የቀበሌው አርሶ አደሮች በመስኖ ልማት ስራቸው ውጤታማነት መሰረት የሆነውን የምንጭ ውሃ ለማጎልበት 8ኛው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ላይ የተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃና እንክብካቤ ስራዎችን በከፍተኛ መነቃቃትና ተነሳሽነት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በገንደ ገበሬ ገጠር ቀበሌ የግብርና ልማት ሰራተኛ የሆኑት አቶ ቦጋለ አባይነህ እንደገለጹት በዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ በቀበሌው 3.5 ኪ.ሜ የውሃ መሄጃ ካናል ጥገና፣ 2 ምንጮችን የማጎልበት ስራ፣ 1 ኪ.ሜ ጋራ ላይ እርከን፣ 1 ኪ.ሜ የመንገድ ጥገና እና 150ሜ/ኪ የኩሬ ጥገና ለመስራት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱንና እስካሁን ባለው አፈጻጸም ደግሞ አራቱ እቅዶች ሙሉ በሙሉ መጠናቀቃቸውን እና የኩሬ ጥገና ስራው ብቻ ታቅዶ ከነበረው 150ሜ/ኪ 1000ሜ/ኪ የሆነው መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
    በአጠቃላይ ከእቅዱ አንጻር 90% የሚሆነውን ስራ ማጠናቀቃቸውን የሚገልጹት አቶ ቦጋለ ይህም ሊሆን የቻለው ቀበሌው አርሶ አደሮች የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ በመስራታቸው ከማንም በላይ የሚጠቀሙት እራሳቸው መሆናቸውን በአግባቡ በመረዳታቸውና ከልባቸው በመስራታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
    የቀበሌው ሊቀ መንበር አቶ ዘከሪያ መሐመድ በበኩላቸው የገንደ ገበሬ አርሶ አደሮች የዘንድሮውን የተፋሰስ ልማት ስራ ከወትሮው በተለየ መልኩ በከፍተኛ ተነሳሽነትና ቁጭት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸው ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ ከዚህ በፊት ከሰሩት የተፋሰስ ልማት ስራ ተጨባጭ ውጤት በማግኘታቸው ነው ብለዋል፡፡ አብዛኛው የቀበሌው አርሶ አደሮች የመስኖ ተጠቃሚዎች እንደሆኑ የሚገልጹት ሊቀመንበሩ በቀበሌው ደርቀው የነበሩ 7 ምንጮች ባለፉት ዓመታት የተፋሰስ ልማት ስራ በመሰራቱ ሙሉ በሙሉ ምንጮቹ ተመልሰው የአርሶ አደሩን የመስኖ ልማት ስራ እያገዙ ይገኛሉም ነው ያሉት፡፡
    የኩሬ ጥገና ስራ ላይ ያገኘናቸው የቀበሌው አርሶ አደር አቶ ረሺድ አሊ በበኩላቸው ባለፉት 5 ዓመታት ኩሬው በደለል በመሙላቱ ምክኒያት ለመስኖ የሚሆን ውሃ ማከማቸት አለመቻላቸውንና በዚህም ምርትና ምርታማነታቸውን በሚፈልጉት መጠን ማሳደግ አለመቻላቸውን ገልጸው ከዚህ በኋላ ግን ኩሬው በአግባቡ በመጸዳቱ በቂ ውሃ በማቆር የተሸለ ምርት ለማምረት ሌት ተቀን እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡