የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የበጀት ኢኮኖሚ እና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከአስተዳደር ምክር ቤት የህዝብ ክንፍ ጋር የድሬዳዋ አስተዳደር የ2015 በጀት አመት ረቂቅ በጀት ዙሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡

    በምክር ቤቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የአስተዳደር ምክር ቤት የበጀት ኢኮኖሚ እና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አይናለም ተዘራ ባደረጉት ንግግር የሚመደበው በጀት በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውል የተለያዩ ተቋማት የፋይናንስ አጠቃቀምን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ከፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ጋር በመሆን የተቀናጀ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው የህዝብ ክንፍ አባላቱም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ከበጀት አፀዳደቅ እስከ አፈፃፀም ለታቀደለት አላማ መዋሉን መከታተል እንደሚኖርበት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
    በመቀጠልም የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አይናለም ተዘራ አያይዘውም እንደገለጹት በአስተዳደሩ የ2014 የበጀት አፈጻጸም ግምገማና የ2015 ረቂቅ በጀት ላይ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎችና ከፍተኛ ባለሞያዎች ጨምሮ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ አመራሮች አስረጂነት የድሬደዋ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ እና የምክር ቤቱ ምክትል አፈጉባኤ በተገኙበት ውይይት መደረጉንና ረቂቅ በጀቱ በአስተዳደሩ ምክር ቤት ቀርቦ ከመጽደቁ በፊት ለህዝብ ክንፍ ቀርቦ ውይይት እንዲደረግበት የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመቀጠልም የድሬዳዋ አስተዳደር የ2015 አመት ረቂቅ በጀትን የፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ምክትል ቢሮ ሀላፊ አቶ ግርማ ተሰማ እና የፕላንና ኢኮኖሚ ልማት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ሃይለማሪያም ዳዲ ቀርቧል፡፡
    በቀረበው ረቂቅ በጀት ላይም የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት ተደርጎበት መድረኩ ተጠናቋል፡፡