የድሬዳዋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በባቡር ዘርፍ በምስራቅ አፍሪካ የልቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ እንደሚገኝ ተገለፀ

የኢፌድሪ ማዕድን ሚኒስተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ከድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀርና ከአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በጋራ በመሆን በድሬዳዋ አስተዳደር እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን እየጎበኙ ሲገኙ፤ በከሰዓቱ መርሀ ግብርም እንግዶቹ የድሬዳዋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅን ጎብኝተዋል።

በዚህም በኢስት አፍሪካ እስኪልስ ፎር ትራንስፎርሜሽን ኤንድ ሪጅናል ኢንተርግሬሽን ፕሮጀክት 14 ሚልየን 850 ሺ ዶላር ተበጅቶለት እየተተገበረ የሚገኘውን ፕሮጀክት ተመልክተዋል።

በፕሮጀክቱ የድሬዳዋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅን በባቡር ዘርፍ፣ በኤሌክትሮ መካኒካል እና በሜታል ኢንጂነሪንግ ዘርፍ የልዕቀት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራም ይገኛል።

የፕሮጀክቱ የኮንስትራክሽን ስራው በ5 መቶ 35 ሚሊየን ብር እየተሰራ ሲሆን በውስጡም የተማሪዎች ማደሪያ ዶርም የመለማመጃ ወርክ-ሾፕ፣ ቤተ-መፅሐፍትና ካፍቴሪያን አካቷል።

በአሁኑ ሰአትም የስራው ሂደት 81 ፐርሰንት የደረሰ ሲሆን በሚቀጥለው ወርም ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ፕሮጀክቱ በስራ ሂደት ከ250 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል።

በኤደን ሳሙኤል

ፎቶ:- አገኘው ሸዋረጋ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *