በድሬዳዋ አስተዳደር “ከቃል እስከ ባህል” በሚል የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ የቅድመ ጉባኤ ማጠቃለያ ኮንፍረንስ ተካሄደ።
በዚህም በመድረኩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ለኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን በማስተላለፍ፤
“ከቃል እስከ ባህል” በሚል እሳቤ የብልፅግና ፓርቲ ለህዝብ የገባውን ቃል በተጨባጭ ከመተግበር ባለፈ የኢትዮጵያን ህልም እውን ለማድረግ የህዝብ ፍላጎትና ስሜትን በመረዳት ምላሽ የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በአስተዳደራችም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ አመራሮች የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነታቸውን አጠናክረው ለውጡን ዳር ለማድረስ ነዋሪው ለረጅም ዓመታት ሲያማርር እና ሲያነሳቸው የነበሩትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መፍታት መቻሉን ከንቲባ ከድር ገልፀው፤ ይህም ፓርቲው ለነዋሪው የገባውን ቃል በተግባር ያሳየበት መሆኑን ተናግረዋል።
በአስተዳደራችን ደረጃ የታለመውን የፍቅርና የብልጽግና ተምሳሌት ራዕይ እውን ለማድረግ የሁሉም የነቃ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ክቡር ከንቲባ ከድር ጠቁመው፤ ይህ ኮንፍረንስ የአባላቱን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ እና የላቀ ሀሳብን ለማስታጠቅ ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።
በአጠቃላይም በአስተዳደራችን በሁሉም ዘርፎች እየተከናወኑ የሚገኙ ውጤታማ ስራዎችን በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር አመላክተው፤አስተዳደራችንን በምስራቅ ኢትዮጵያ የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይን ከግብ ለማድረስ በቁርጠኝነት መረባረብ ይገባል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በኤደን ሳሙኤል
ፎቶ፦አገኘሁ ሸዋረጋ


