የድሬዳዋ አስተዳደር የ 2017 በጀት ዓመት የ 2 ተኛ ሩብ አመት የማዘጋጃ ቤታዊ ፣ የሴክተር ተቋማት ፣ የከተማና ገጠር ወረዳዎች የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ መድረክ በዛሬው እለት እየተካሄደ ሲሆን በሪፖርቱ ከካይዘን ትግበራ ሀብት ብክነት ጋር ተያይዞ በአምራች ኢንዱስትሪዎችና በአገልግሎት ዘርፍ በካይዘን ትግበራ 5 ሚሊዮን ብር ለማዳን ታቅዶ 14,202,900 የሚገመት ሀብት ከብክነት ለማዳን የተቻለ ሲሆን ወደ ካይዘን ትግበራ ለማስገባት በተመረጡ ተቋማት እና አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ለሚገኙ 476 አመራርና ሰራተኞች በካይዘን ፍልስፍና እና አተገባበር ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠናም መስጠት ተችሏል ።
ከኢንቨስትመንት እና ንግድ ልማት ጋር ተያይዞ በኢንቨስትመንት ፍሰት በስድስት ወሩ ለ 1,934 ስራ ፈላጊዎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የስራ እድል ሊፈጥሩ የሚችሉ 3 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 245 ባለሀብቶችን መሳብ እንደተቻለና ዘመናዊ ፍትሀዊ እና በውድድር ላይ የተመሰረተ የንግድ ስርአትና ግብይት ማስፈንን በተመለከተ የበይነ መረብ ( ኦንላይን ) የንግድ ምዝገባ እና ፍቃድ አሰጣጥ ሽፋንን 97 በመቶ የማድረስ ፣ የንግድ ምዝገባ እና ፍቃድ መስጫ ጣቢያዎችን የድህረ ፍቃድና ሪጉላቶሪ ስራዎችን ሽፋን 100 % ማድረስ ተችሏል ።
የቱሪዝምና ባህል ልማት በመረጃ የበለፀገ ማህበረሰብን ለመፍጠር በግማሽ አመቱ 43,950 የማህበረሰብ ክፍሎች የንባብ አገልግሎት እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን በባህል ረገድ 559 የመረጃ ሀብቶችን የማሰባስብ እና 9,000 የመረጃ ሀብቶች የማደራጀት እንዲሁም 9 የመረጃ ሀብቶችን በእቅዱ መሰረት የማሰራጨት ስራ ተሰርቷል ። የሀገር ውስጥ እና የውጪ ቱሪስቶችን ፍሰት በማሻሻል 106,609 የሀገር ውስጥ እና 17,436 የውጪ ቱሪስቶች ወደ አስተዳደሩ የመጡ ሲሆን ከነዚህም 1,100,650,000 ብር ከሀገር ውስጥ የቱሪስት ፍሰት እና 192,300,000 ከውጪ ቱሪስት ፍሰት ሀብት ለአስተዳደሩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማስገኘታቸውም ነው በሪፖርቱ ላይ የተገለፀው ።
የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተቀባይነት ሽፋን በተመለከተ በበጀት አመቱ መነሻ ላይ 40 % ተደራሽ የነበረውን የአገልግሎት ዘርፍ በግማሽ አመቱ ወደ 48 % ለማሳደግ ታቅዶ ወደ 43 % ማሳደግ የተቻለ ሲሆን ይህም ከግማሽ አመቱ እቅድ አንፃር የ 90 % አፈፃፀም ላይም እንደሚገኝ ተገልፆል ። ሌላው የቅድመ ወሊድ ክትትል ከ 12 ሳምንት በፊት ያገኙ ነፍሰጡር እናቶች ሽፋን በበጀት አመቱ መጀመሪያ ከነበረበት የ 37 % ሽፋን በግማሽ አመቱ ወደ 41 % ለማሳደግ ታቅዶ 35.2 % ማሳደግ የተቻለ ሲሆን የእቅድ አፈፃፀሙም 86 % የአፈፃፀም ደረጃ ላይም እንደሚገኝ ተገልፆል ።
HIV ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የፀረ HIV መድኃኒት የሚወስዱ እናቶች ሽፋን በተመለከተ በበጀት አመቱ መነሻ የነበረውን የ 100 % የአገልግሎት ሽፋን ወደ ነበረበት ለማስቀጠል የተያዘው እቅድ የአገልግሎት ሽፋኑን 126 % ማድረስ በመቻሉ ከ 100 % የእቅድ አፈፃፀም ተመዝግቧል ። የቲቢ እና የስጋ ደዌ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ጋር ተያይዞ በበጀት አመቱ መጀመሪያ የነበረበትን የ 100 % ልየታ ሽፋን በግማሽ አመቱ ባለበት 100 % ለማስቀጠል ታቅዶ 107 % የልየታ ሽፋን ላይ በመድረሱ ከእቅድ በላይ ማከናወን ተችሏል ።
ከትምህርት ልማት ጋር ተያይዞ የተደራጀና ውጤታማ የሆነ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች ወተመህ አደረጃጀት ከመፍጠር አኳያ በ 90 መንግስት ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በ 35 የግል ትምህርት ቤቶች የወተመህ አደረጃጀት የተደራጀ ሲሆን በ 44 ትምህርት ቤቶች ላይ በአዲሱ ማንዋል መሰረት የተጓዳኝ ልማት አደረጃጀት እንዲኖራቸው ታቅዶ በእቅዱ መሰረት 44 ቱም ትምህርት ቤቶች ላይ መደራጀት ተችሏል ።
የሴቶች እና ህፃናት ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት አኳያ 7,100 ሴቶችን በማደራጀት ጥቅማቸውን እንዲያስጠብቁ ለማድረግ ታቅዶ 7,650 ሴቶችን ( 107.7 % ) ማደራጀትም የተቻለ ሲሆን በግማሽ አመቱ ጥቃት የደረሰባቸውን 18 ሴቶች እና ህፃናት በአንድ ማእከል የአገልግሎት መስጫ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ የስነ-ልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ መደረጉንም ነው በሪፖርቱ ላይ የተገለፀው ።
የከተማውን የመጠጥ ውሀ አቅርቦት ከማስፋፋትና ከማሳደግ አንፃር የመልካ መጠጥ ውሀ የሲቪልና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ግንባታ 60 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ 65.8 በመቶ ማድረስ የተቻለ ሲሆን የእቅድ አፈፃፀሙም 109.6 እንደሆነና የከተማውን የውሀ አቅርቦት ችግር ለመፍታት በአማካሪ ድርጅት የተከናወነ የ 30 አመት የውሀ መገኛ ጥናት እና ስራዎችን 80 % ማከናወን እንደተቻለም ነው በሪፖርቱ ላይ የተገለፀው ።
በአለማየሁ አበበ
ፎቶ :- አገኘው ሸዋረጋ


