የድሬዳዋ አስተዳደር የ 2017 በጀት ዓመት የ 2 ተኛ ሩብ አመት የማዘጋጃ ቤታዊ ፣ የሴክተር ተቋማት ፣ የከተማና ገጠር ወረዳዎች የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ መድረክ በዛሬው እለት መካሄደ የጀመረ ሲሆን ሪፖርቱንም የአስተዳደሩ የፕላንና ኢኮኖሚ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት አቶ ሀይለማርያም ዳዲ ያቀረቡ ሲሆን ሪፖርቱንም መነሻ በማድረግ የተለያዩ ሀሳብ አስተያየቶች ተነስተዋል ።
በድሬዳዋ አስተዳደር የቅዳሜ እና እሁድ ገበያ ላይ ከመደበኛው ግብይት አንፃር ብዙም ልዩነት እንደ ሌለው ፣ ከነዳጅ አቅርቦት አንፃር እጥረቶች እንዳሉና አሁን ላይ ነዳጅ በብላክ እየተሸጠ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አሽከርካሪዎች ከፍተኛ ቅሬታ እያነሱ መሆኑንም ነው የተገለፀው ። ከዚህ በተጨማሪም ከትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ አንፃር በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም በትራንስፖርት ላይ የወጣው ታሪፍ ግን ውጤት እያመጣ አለመሆኑም ተገልፆል ።
በመኖሪያ ቤቶች ብሎም በአካባቢያችን ተግባራዊ የሚደረጉ የከተማ ግብርናዎች በስፋት እንዲሰሩ የሚደረጉበት አማራጮች መፈጠር እንዳለባቸው እንዲሁም ከትምህርት ጋር ተያይዞ በወረዳ 0 7 ላይ ያለው የሀጂ አብዱላሂ ኦክሰዴ መታሰቢያ ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እየተከታተሉ አለመሆኑም የተገለፀ ሲሆን በአስተዳደሩ በርካታ የልማት ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም ነገር ግን የካፒታል ፕሮጀክቶች ላይ መዘግየቶች እንደሚስተዋሉ ገልፀው ከገጠር ስራ እድል ፈጠራ አንፃር እንዲሁም የገበያ ትስስር ከመፍጠር አንፃር ውስንነቶች እንደሚስተዋሉና በቀጣይ በትኩረት መሰራት እንደሚገባም ነው የተገለፀው ።
ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የመንግስት ሰራተኞች የሚሰሩ የድጎማ ስራዎች በምን አግባብ እየተሰራ እንዳለ ፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ፍልሰት ለመቀነስ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ፣ አስተዳደሩን ፅዱ ውብ እና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ ይቻል ዘንድም ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም ነገር ግን አሁንም የፅዳት ስራዎች በስፋት መሰራት እንዳለበትም ተገልፆል ።
ከነዳጅ ጋር ተያይዞ አሁን ላይ በአስተዳደሩ የብላክ ማርኬት ግብይቶች በስፋት እንደሚስተዋሉና እነዚህንም ተግባራት የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎች መስራት እንደሚገባ እንዲሁም ከፍጆታ አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉትንም ችግሮችን ለመፍታት መስራት እንደሚገባ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጁሀር ተናግረው የንባብ ባህልን ማዳበርም እንደሚገባና አዲሱ ቄራ ላይ ያሉትን ችግሮች በመፍታት በቀጣይ ስራ የማስጀመር ስራዎች መሰራት እንዳለባቸውም ነው ክቡር አቶ ከድር ጁሀር ያስታወቁት ።
ከስራ ክህሎት ጋር ተያይዞ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም በቀጣይ በከተማም ሆነ በገጠር ሰፋፊ ስራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ የተገለፀ ሲሆን ከግብርና ውሀ ማእድንና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ጋር ተያይዞ ከእንስሳት እና እርባታ ጋር ተያይዞ ወደ ስራ ለሚገቡ ባለሀብቶች አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ እንዲሁም ከትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ጋር ተያይዞ ታሪፍ ቢወጣም ነገር ግን የወጣው ታሪፍ ተግባራዊ እንዳልሆነና ይህም መስተካከል እንዳለበትም ነው ክቡር አቶ ከድር ጁሀር ያስታወቁት
ከስራ እድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ የስራ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ስራ ብቻ መሆን እንደሌለበትና ሴክተር ተቋማት እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በዚህ ዙሪያ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ሀርቢ ቡህ ተናግረው ከነዳጅ ጋር ተያይዞ አሁን ላይ በከተማዋ የተለያዩ ነዳጅ ማደያዎች ላይ ነዳጅ እንዳለና በነዳጅ ዙሪያ ህገ-ወጥ ስራዎችን የሚሰሩት ላይ ህጋዊ እርምጃ በመወሰድ ላይ መሆኑንም ነው አቶ ሀርቢ ቡህ ያስታወቁት ።
በእስተዳደሩ የጎዳና ተዳዳሪዎች እና የአይምሮ ህመምተኞች ቁጥር እየጨመረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይህንንም ችግር ለመፍታት በትኩረት መሰራት እንዳለበት ተናግረው ከተማዋን ፅዱ እና ውብ ከማድረግ ጋር ተያይዞም ቢሆን ቀጣይነት ያላቸው ስራዎች ሊሰሩ እንደሚገባም ነው አቶ ሀርቢ ቡህ በእለቱ የተናገሩት ።
በአለማየሁ አበበ
ፎቶ :- አገኘው ሸዋረጋ


