የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ “ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ቃል ከተለያዩ ሀገራት የመጡ እህት ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል፡፡
የቱርክ ኤኬ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ዛፈር ሲራካያ በጉባኤው ላይ ባስተላለፉት መልእክት፤ ቱርክ ከኢትዮጵያ ጋር የቆየ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላት ገልጸው ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የታሪክ ማህደር ልዩ ስፍራ ያላት አገር ናት ያሉት ምክትል ሊቀመንበሩ፤ የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት እና የብዝሃነት መኖሪያ ናት ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ አሁን እየታየ ያለው ለውጥና እድገት በትብብር በመስራትና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
የዩናይትድ ሩስያ ፓርቲ ሱፕሪም ካውንስል ቢሮ አባልና የሩስያ ፌዴሬሽን ሴናተር አንድሬ ክሊሞቭ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያና ሩስያ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ታሪካዊና በበርካታ መስኮች ላይ የተመሰረተ አጋርነት እንዳላቸው ጠቁመዋል።
የሁለቱን ሀገራት አጋርነት በሁለትዮሽና ባበለብዙ ወገን በተለይም ብሪክስንና የአፍሪካ ሩስያ አጋርነት መድረክን በመጠቀም ለማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የካዛኪስታኑ አማናት ፓርቲ እና የሀገሪቱ ፓርላማ የታችኛው ምክር ቤት አባል ሳማት ኑር ታተዛ በመልእክታቸው፤ የኢኮኖሚ ልማትና ማህበራዊ ዋስትናን ለማስፈን የታለመው ሰፊ ማሻሻያ ኢትዮጵያ ቁልፍ የመረጋጋትና የብልጽግና ማዕከል እንድትሆን አስችሏታል ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጽያ የለውጥና የዕድገት ምልክት ነው ያሉ ሲሆን፤ ፓርቲው በቀጣይ የስራ ዘመኑ ስኬት እንዲገጥመው እመኛለው በማለትም መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
EBC


