የብልጽግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በፓርቲው ሁለተኛ ጉባኤ የተላለፉ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በመግለጫቸው ብልጽግና ፓርቲ በሁለተኛ መደበኛ ጉባኤው ከአንደኛው እስከ ሁለተኛው መደበኛ ጉባኤው ያሉትን ስራዎች መገምገሙን ገልፀዋል፤ በዚህም የተላለፉ ውሳኔዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል። ሃላፊው በኢትዮጵያ በዲፕሎማሲና በውጭ ግንኙነት ዘርፍ የተገኙ ሀገራዊ ስኬቶችና ውጤቶችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተሻለ ስኬት እየታየበት እንደሚገኝ የፅ/ቤት ሃላፊው ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ የውጭ ግንኙነት ከመሰረቱ የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ገልጸው በተለይ በጥንታዊው የአክሱም ዘመን በንግድና በሃይማኖታዊ ጉዳዮች የተጀመረው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ታሪክ ዛሬ ላይ ጠንካራ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነቶችን በመፍጠር እያደገ መምጣቱን አንስተዋል።
አቶ ኢብራሂም አክለውም ኢትዮጵያ ቀደምት ሀገር በመሆኗ ሀገር አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ተቋማትን በማቋቋምም ቀዳሚ ከሚባሉት ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ናት ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጉዞ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከፍታ እና ዝቅታ ሲያስተናግድ መቆየቱንም አንስተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ማዕቀፍ ታዲያ በለውጡ ብሔራዊ ጥቅማችንን ማስጠበቅና ሉዓላዊነታችንን ማስከበር በሚያስችል መልኩ ሪፎርም ተደርጓል ነው ያሉት።
በዚህም የውጭ ግንኙነታችን በቀዳሚነት ሰላምና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ላይ ያተኮረ እና ባለብዙ ወገንና የሁለትዮሽ ላይ ያተኮረ፣ የፖለቲካ ማእቀፍ ላይ ማዕከል ያደረገ ዲፕሎማሲ እንዲሁም ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን እንደ አንድ ትልቅ ማዕቀፍ አድርጎ የያዘ የውጭ ግንኙነት የዲፕማሲው ዋና ዋና የትኩረት መስኮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን ማጠንጠኛው ከሀገራዊ ፍላጎቶችና ተጨባጭ ሁኔታዎች የሚነሳ ነው ያሉት ኃላፊው አሁን ላይ አለም ፊቱን ወደ ኢትዮዽያ በማዞሩ በኢንቨስትመንት ፣ በወጪና ገቢ በንግድ ፣ ተጠቃሚ ሆነናል ብለዋል። ቀዳሚ ዓላማውም በሁሉም መስክ ብሔራዊ ጥቅምን ማረጋገጥና ሉዓላዊነትን ማስከበር መሆኑን ገልጸዋል።
የፖሊሲ ማዕቀፉ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ ትኩረት እንደሚሰጥ ጠቅሰው፤ ከዚህ ባለፈ ወደ አፍሪካ ብሎም ወደ ዓለም አደባባይ በባለብዙ ወገንና በሁለትዮሽ ግንኙነት እየሰፋ ይሄዳል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ታሪክ በየዘመኑ ብዙ ፈተናዎች ተሻግራለች ያሉት አቶ ኢብራሂም በየዘመኑ ሲደርሱባት የነበሩትን ልዩ ልዩ ጫናዎች ተቋቁማ በሠራችው የዲፕሎማሲ ሥራ ከራሷ አልፋ ለአፍሪካውያንና ሌሎችም ጥቁር ሕዝቦች ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቷንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን፣ መንግሥትና ወዳጅ ሀገራት ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብና ተጋድሎ ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የሆነውን ጫና ተሻግራ ሉዓላዊነቷን፣ የግዛት አንድነቷንና ብሔራዊ ጥቅሟን አስጠብቃ ጸንታ መቀጠሏንም ጨምረው አብራርተዋል።
Diretv


