በድሬዳዋ ከተማ የጎዳና ላይ ልመናን እና ጎዳና ተዳደሪነትን እንዲሁም በጎዳና ላይ የሚከናወኑ አልባሌ ተግባራትን ለመከላከል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊረባረብ እንደሚገባ ተገለጸ

#DGC የካቲት 18/2017

በዛሬው ዕለት በድሬዳዋ አስተዳደር የጎዳና ተዳዳሪነትን እንዲሁም የጎዳና ላይ ልመናን ለመቆጣጠር የሚደረጉ ድጋፎችን ለመወሰን የተዘጋጀ ረቂቅ ደንብን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመተግበር ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሄደ፡፡

በመድረኩ የድሬዳዋ አስተዳደር ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀ

ኃላፊ ወ/ሮ ሁክሚያ መሀመድ በድሬዳዋ ከተማ የጎዳና ተዳዳሪነትና የጎዳና ላይ ልመና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልፀው፤ ይህም በከተማው የእለት ተዕለት የማህበራዊ ህይወትና የንግድ እንቅስቃሴ ላይ እንዲሁም የመሰረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት፣ የጤና አጠባበቅ፣ የአካባቢ ጥበቃና ፅዳት ላይ አሉታዊ ተፅኖ እያሳደረ መምጣቱን አብራርተዋል፡፡

ወ/ሮ ሁክሚያ አያይዘውም የዛሬው መድረክ በዋነኝነት የወጣውን ደንብ ተግባራዊ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ስራዎችን ለመስራት ያለመ የውይይት መድረክ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ጎዳና ተዳዳሪዎችንና ለምኖ አዳሪዎችን የመከላከል ስራ መሰራቱን ወ/ሮ ሁክሚያ አስታውሰው አሁንም እንደ አስተዳደር የተከለከሉ ቦታዎች ላይ ልመናም ሆነ አልባሌ ተግባር ለመከላከል ደንብ መዘጋጀቱንና ደንቡንም ተግባራዊ ለማድረግ ስራዎችንም ካለማቋረጥ ወጥ በሆነ መልኩ መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

በዚህም ለአረጋውያን መቆያ መዘጋጀቱን፣ ለአእምሮ ህመምተኞችም የህክምና ድጋፍ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎች እንደሚፈጠሩ ጠቅሰው ከዛ በተጨማሪ መስራት የሚችሉ ነገር ግን ኑሮአቸውን በጎዳናና በልመና ላይ ላደረጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ከስራ ክህሎት ቢሮ ጋር በመተባበር አጫጭር ስልጠናዎችን በማመቻቸት ወደ ስራ የሚገቡበትን ሁኔታ የሚፈጠር መሆኑን ወ/ሮ ሁክሚያ ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም በድሬዳዋ አስተዳደር የጎዳና ላይ ልመናን፣ ጎዳና ተዳደሪነትንና በጎዳና ላይ የሚከናወኑ አልባሌ ተግባራትን ለመከላከል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊረባረብ እንደሚገባ ኃላፊዋ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉት ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው ለደንቡ ተግባራዊነት ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀትና በመናበብ ስራዎችን እንደሚያከናውኑ አመላክተዋል፡፡

በኤደን ሳሙኤል

ፎቶ፡- ቴድሮስ ልዑልሰገድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *