የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሙኒኬሽን ዘዴ ለሥራ ተነሳሽነት የሚፈጥሩ ልምዶችን በማካፈል ላይ ያተኮረ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡
ጽ/ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላለፉት ሰባት ዓመታት ለየት ባለ መንገድ ግልጽነት እና ተደራሽነትን ዓላማ ያደረገ የኮሙኒኬሽን ዘዴ ሲያከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሷል፡፡
ይህ የኮሙኒኬሽን ዘዴም በልዩ አተያይ ሐሳቦችን፣ ለሥራ ተነሳሽነት የሚፈጥሩ ልምዶችን እና ተግባራትን በማካፈል ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከክልሎች የሚገኙ የሥራ ሪፖርቶችን ለሌሎች የተነሣሽነት ምንጭ እንዲሆኑ በማሰብ አልፎ አልፎ እንደሚያጋሩም ጠቁሟል፡፡
ይህም የክልሎች የሥራ ለውጦች ጎላ ብለዉ እንዲታዩ፣ ምርጥ ተመክሮዎች እና ስኬቶች ከፍ ተደርገው እንዲሰሩ እንደሚረዳም አስገንዝቧል፡፡
ይሁንና ከታችኛው የአስተዳደር እርከን ጀምሮ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ መረጃዎች በሚፈሱበት ሂደት አንዳንድ ትክክል ያልሆኑ አቀራረቦች በተለያየ እርከን በሪፖርቶች ሊካተቱ መቻላቸውን ትናንትና በተጋራው መልዕክት መመልከቱን ጽ/ቤቱ አስታውቋል፡፡
ከዚህ አንፃር በትናንትናው ዕለት በተጋሩ ምስሎች ውስጥ የተወሰኑ ምስሎች ከመስክ ከተገኙ እውነተኛ ፎቶዎች ጋር ተቀላቅላቅለው ከክልል ከነበረ ልውውጥ እስከ ፌደራል ደረጃ መድረሳቸውን ገልጿል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ይሄን መሰል የመረጃ ፍሰት ስህተት ዳግም እንዳይፈጸም ተገቢ ርምጃዎችን በመወሰድ ላይ መሆኑን በማንሳት ፤ ምስሎቹን የያዘው ልጥፍ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ገጽ መነሳቱን አመላክቷል፡፡
ጉዳዩን ጽ/ቤቱ እንዲመለከተው እና ርምት እንዲወሰድ ያሳወቁ ዜጎችን በማመስገንም ፤ ትክክለኛውን መረጃ እና አቀራረብ የያዙ የተምሳሌታዊው ምርት ሥራ ዘገባዎች በሚዲያዎች እንደሚቀርቡም በማኀበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል፡፡


