የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የሚሳተፉና የሚመረጡበት የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር በድሬዳዋ በነገው እለት ይጀመራል

ውድድሩን አስመልክቶ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌድሬሽን የቴክኒካል ዳይሬክተር አትሌት አሸብር ደምሴና የአስተዳደሩ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አህመድ አብዶ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

ለ 7 ተከታታይ ቀናት የሚካሄደው አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ዋናው አላማ በናይጄሪያ ለሚደረገው የአፍሪካ የወጣቶች አትሌቲክስ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን መምረጥና የውድድር ዕድል መስጠት እንደሆነ ተነግሯል።

ከግንቦት 18 እስከ 24 በሚከናወነው ሻምፒዮና ላይ ከ10 ክልሎች እና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ45 በላይ ክለቦች ይሳተፋሉ።

ከ20 ዓመት በታች በሁለቱም ፆታ 825 አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን 370 አትሌቶች ደግሞ ከ18 ዓመት በታች ውድድር ላይ የሚሳተፉ ሲሆን በአጠቃላይ 1192 አትሌቶች በውድድሩ የሚሳተፉ ይሆናሉ።

በውድድሩ ከ 1ኛ እስከ 3ኛ ለሚወጡ ተወዳዳሪዎች የገንዘብና የማበረታቻ ሽልማት እንደሚሰጥም ታውቋል።

በድሬዳዋ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውድድሮች በአስተዳደሩ ለሚገኙ ወጣቶች ክለቦች ትልቅ አቅም የሚፈጥር እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ውድድሮችን ለማካሄድ ትልቅ እድል የሚፍጥር መሆኑም ተገልጿል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከነገ ጀምሮ በሚካሄደው የአትሌቲክስ ስፖርት ውድድርም የአስተዳደሩ የስፖርት አፍቃሪያን ቤተሰቦች እና ነዋሪዎች ድጋፋቸውን እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

ሰላም ለማ

ምስል:- ናታን ሸዋንግዛው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *