የአስተዳደሩ ነዋሪ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ከመቅረፍ አንፃር በአዲሱ በጀት አመት በአስተዳደሩ አፅዕኖት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ተገለፀ።

በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የድሬዳዋ አስተዳደር እንደራሴዎች እና የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ተመራጮች ከመረጣቸዉ ህዝብ ጋር የሚወያዩበት የህዝብ ዉክልና ማጠቃለያ መድረክ ተካሄደ።

በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የድሬዳዋ አስተዳደር እንደራሴ የሆኑት አቶ አብዱልጃዋድ መሀመድ በመድረኩ ላይ ተመራጮችና የህዝብ ዉክልና ያላቸዉ አካላት ከመረጧቸዉ ህዝብ ጋር በልማት፣በመልካም አስተዳደር፣የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን አስመልክተው ሀሳባቸውን በማድመጥ የህዝብ ዉክልና የሚወጡበት ዉይይት መሆኑን ገልፀዋል።

በመድረኩ ከህብረተሰቡ ከተውጣጡት ተሳታፊዎች ሀሳቦችና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን በጤና ረገድ ፣በትምህርት ዘርፍ ፣ በመንገድ መሰረተ ልማት እጥረት፣የሴቶችን ተሳትፎ ከማሳደግ አንፃር ፣ ከሰዎች ፍልሰት እና እንዲሁም ሌሎች የመሰረተ ልማት ችግሮችና ከስራ እድል ፈጠራ አንፃር ያሉ ክፍተቶችንና ቢስተካከሉ የሚሏቸውን ጥያቄዎችን አንስተዋል።

በተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የድሬዳዋ አስተዳደር እንደራሴዎች የሆኑት ዶ/ር ቢፍቱ መሐመድና አቶ አብዱልጀዋድ መሀመድ እንዳሉት የተነሱ ጥያቄዎች በቀጣይ በአስተዳደሩ በሚሰሩ ስራዎች ዉስጥ በእቅድ ተካተዉ የሚፈፀሙ መሆናቸዉን ገልፀዉ በድሬዳዋ ያለውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግና ለማስቀጠል መንግስት ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡም የራሱን ሚና መወጣትና ተሳትፎ ማድረግ ያስፈልገዋል ብለዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ከሪማ አሊ በበኩላቸው መንግስትና ፓርቲያቸው የገባዉን ቃል ተፈፃሚ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዉ ያሉትን ችግሮች በከተማና በገጠር በተጨባጭ በመመልከትና ያሉትን ችግር በመለየት የሚፈቱ መሆኑን ገልፀዋል ።

በመድረኩ ማጠናቀቂያም ለ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለሚሹ አካላት ድጋፍ ተደርጓል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *