እናት ሀምዲያ መሀመድ
የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ያጠናቀቀውን የአቅመ ደካማ ቤት በዛሬው ዕለት ቁልፉን ለባለቤቱ አስረከበ።
ቢሮው የራሳቸው 3 ልጆች በተጨማሪ ደግሞ የሚያሳድጓቸው 2 ልጆች በድምሩ የ5 ልጆች እናት የሆኑትን የእናት ሀምዲያ መሀመድ ቤትን ዘመናዊ እና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ገንብቶ በማጠናቀቅ አስረክቧል።
በዚህም በመርሃ-ግብሩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ብሩክ ፈለቀ ለአዲሱ አመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን በማስተላለፍ ቤቱ በክረምት የበጎ ፍቃድ ስራዎች እንደተገነባ ገልፀዋል።
ቤቱን በአንድ ወር ውስጥ ገንብቶ በማጠናቀቅ በአዲስ ዓመት በዓል ቤቱን በማስረከባቸው አቶ ብሩክ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀው፤ በቀጣይም ቢሮው አቅመ ደካማ ወገኖችን የማገዝ ስራ አጠናክሮ እንደሚሰራ አመላክተዋል።
በመጨረሻም አቶ ብሩክ ቤቱ እንዲገነባ የበኩላቸውን ድጋፍ እና አስተዋፆ ላበረከቱት ወረዳ 03 እና 05 ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
እናት ሀምዲያ መሀመድ በበኩላቸው በቤት ችግር ልጆቻቸው ተበታትነው እቃቸውም በየጎረቤት አስቀምጠው እንደነበረ ጠቅሰው የመንግስት ኮምኔኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ላደረገው በጎ ተግባር በማመስገን “አዲሱን አመት በደስታ አስጀመራችሁኝ ልጆቼንም ስለሰበሰባችሁልኝ በማለት ስሜታቸውን አጋርተዋል”።
የወረዳ 03 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ምትኩ ሁነኛው እና የወረዳ 05 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አብርሀም ይመር እናት ሀምዲያ በቤት ችግር ከልጆቿ ጋር በመሆን ብዙ ችግር እንዳሳለፈች ገልፀው ዛሬ ላይ የቤት ባለቤት በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።


