የድሬዳዋ አስተዳደር ሴቶች ህፃናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከቼንትሮ አዩቲ ፔር ሊ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር አዲስ ዓመትን በማስመልከት ለችግረኛ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተበርክቷል።
በዚህም በመርሃ-ግብሩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ሴቶች፣ ህፃናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሁክሚያ መሀመድ በድሬዳዋ አስተዳደር በገጠርም በከተማም ለሚገኙ አቅመ ደካማ ወገኖች ድጋፍ እየተበረከተ መሆኑን ገልፀው፤ በዛሬው ዕለትም ችግረኛ ተማሪዎች በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ከትምህርት እንዳይቀሩ በማሰብ የተደረገ ድጋፍ መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገራችን የጀመረችውን የብልፅግና ጉዞ ለማፋጠን ትምህርት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ወ/ሮ ሁክሚያ ተናግረው ሁሉም ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ በመከታተል ውጤታማ መሆን እንደሚገባቸው የመከሩ ሲሆን፤ የተቸገሩ ተማሪዎችንም መደገፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ቼንትሮ አዩቲ ፔር ሊ ኢትዮጵያ አቅመ ደካማ ወገኖችን እያገዘ የሚገኝ ተቋም መሆኑን የጠቆሙት ደግሞ የቼንትሮ አዩቲ ፔር ሊ ኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ አቶ ፓውሎ ላንቫርዶ ናቸው። አቶ ፓውሎ በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
ድጋፉ የተበረከተላቸው አቅመ ደካማ ወገኖች በበኩላቸው በተበረከተው ድጋፍ መደሰታቸውን በመግለፅ አመስግነዋል።


