የበርካታ ወጣቶችን ህይወት እያሳጣ የሚገኘውን የህገ-ወጥ ፍልሰትና ስደት ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለፀ

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንዲሁም ከዓለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት (ILO) ጋር በመተባበር “ስደት እና ልማት”(Migration and Development) በሚል መሪ ቃል ከተለያዩ ሀገራት የተወጣጡ ተመራማሪዎች እና የመንግስት አካላት በተገኙበት አለም አቀፍ ኮንፍረንስ እያካሄደ ይገኛል።

ኮንፍረንሱ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ይሆናል።

በመድረኩ የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር አለም አቀፍ ኮንፍረንሱ ድሬዳዋ በመዘጋጀቱ የተሰማቸውን ደስታ በመግለፅ፤ ለእንግዶቹ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከንቲባ ከድር ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የበርካታ ወጣቶችን ህይወትን እየቀጠፈ እንደሚገኝ ጠቅሰው ይሄንን ችግር ለመቅረፍ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር እንደሚገባ ገልፀዋል።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም በበኩላቸው በመድረኩ ትኩረታቸውን ስደት ላይ ያደረጉ ምርምሮች ቀርበው ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደሚካሄድ በተጨማሪም ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ምክረ ሀሳቦች እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል።

በዚህ ፕሮጀክት ላይ ከድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር እየሰራ የሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስደትና የፍልሰት ጥናት ማዕከል ዳሬክተር የሆኑት አቶ አበባዉ ማናዬ ፍልሰትና ህገ-ወጥ ስደትን በተመለከተ ግልፅ መረዳት እንዲፈጠር በትኩረት መሰራት እንደሚገባ አመላክተው የችግሩን አሉታዊነት ብቻ ሳይሆን አወንታዊ ጎኖቹም በመለየት መሰራት እንደሚገባው ተናግረዋል።

ስምንት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን ያቀፈ የፍልሰት ማዕከል በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ሊቋቋም መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በድሬዳዋ ዩንቨርስቲ የስትራቴጂክ አጋርነትና አለማቀፍነት ዳይሬክተር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዳዊት ዳንኤል ናቸው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *