ኦል-ብራይት ኢንተርናሽናል ኮሌጅ ድሬዳዋ ካምፓስ በቴክኒክና ሞያ ትምህርት ስልጠና በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን አንድ መቶ ሃያ ተማሪዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ በዛሬው እለት አስመርቋል ።ከተመራቂ ተማሪዎቹ ውስጥ 80 ያህሉ ሴቶች ናቸው ተብሏል።
በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ የአስተዳደሩ ከንቲባ ተወካይና እንዲሁም የከንቲባ ፅ/ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ሀላፊ አቶ ገበየሁ ጥላሁን ባደረጉት ንግግር ኮሌጁ በማስተማር ፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት እንደ አስተዳደር ትልቅ አስተዋጽዖ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
አቶ ገበየሁ አያይዘውም በተለይም አሁን አስተዳደሩን ከአለም እኩል የሚያራምደውን በቴክኖሎጂው ዘርፍም ተማሪዎችን ከማብቃት ባሻገር ለተቋማት መተግበሪያዎችን በማበልፀግ የተለያዩ ተቋማትን በማገዝ ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ተማሪዎቹም በተማሩት ትምህርት ሃገራቸውን በታማኝነት እንዲያገለግሉም አቶ ገበየሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኮሌጁ ዲን አቶ ሚኪያስ ብርሃኑ በበኩላቸው እንዳሉት ኮሌጁ ከተመሰረተ ዛሬ የመጀመሪያውን ዙር ያስመረቀ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ምርቃትም የህዳሴው ግድብ ምርቃት ማግስት መሆኑ ድርብ ድል ነው ብለዋል።
ይህ የምረቃ ለተማሪዎቹ የመጨረሻቸው ሊሆን እንደማይገባ የገለፁት ዲኑ ተመራቂዎች በሙያቸው አገራቸውን እና ህዝባቸውን ለማገልገል የመጀመሪያ ጉዞ የሚጀምሩበት ነው በማለት ለተመራቂዎቹ መልዕክት አስተላልፈዋል ።
ተመራቂ ተማሪዎችም ለዓመታት የለፉበት ትምህርት ለፍሬ በመብቃቱ መደሰታቸውን ገልጸው በቀጣይም በዲግሪ መርኃግብር ለመማር ማቀዳቸውን ገልፀዋል።
በእለቱ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የተለያዩ ሽልማቶች ከኮሌጁ ተበርክቶላቸዋል።


