በድሬደዋ አስተዳደር አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን የአደጋ ስጋት ቅነሳ ስራዎችን በተቋማት የልማት እቅድ ውስጥ ማካተትን በተመለከተ ለሴክተር ተቋማትና ለግል ድርጅቶች ባለሞያዎች እና አመራሮች ስልጠና ተሰጥቷል።
በአደጋ ስጋት ቅነሳ አጠቃላይ በመንግስት ተቋማት የተቀናጀ ስራ በመስራቱ በራስ አቅም በአስተዳደር ደረጃ የአደጋ ቅነሳ ስራዎች በስፋት መከወናቸውን በድሬደዋ አስተዳደር አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን ኮምሽነር አቶ ሱሌማን አሊ ተናግረዋል።
በአስተዳደሩ የሚኖሩ የጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ ማህበረሰቦችን የቅድመ መከላከል ስራዎችን ቀድሞ በመሰራቱ ላለፉት አምስት አመታት የከፋ ችግር በዜጎች ላይ አለመድረሱን አቶ ሱሌይማን ጨምረው አስታውቀዋል።
በድሬደዋ አስተዳደር የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን የአደጋ ስጋትና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡዱን መሪ የሆኑት አቶ ወንደሰን በሪ በበኩላቸው በአስተዳደሩ የቅድመ አደጋ ስጋት ቅነሳ እና የድህረ አደጋ ክስተቶችን መቆጣጠር የተቀናጀ ድጋፍ ስራ ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር ታልሞ የግንዛቤ ማሳደጊያ ስራ በመሰራት ላየሰ መሆኑን ገልፀዋል።
በሀገሪቱ በ2016 ዓ.ም በወጣው አዲስ ፖሊሲ ዙሪያም ስልጠና ተሰጥቷል።ኢትዮጵያ ለጀመረችው ሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚያዊና የልማት እድገት ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎችን በራስ አቅም በሀገር በቀል ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ የተቋማት የድርጅት ሰራተኞች ባለሞያዎችና አመራሮች በተገቢው ልክ ተቀናጅተው ሊያቅዱ እና ሊሰሩ እንደሚገባ በስልጠናው ላይ ተመላክቷል።
በድሬዳዋ አስተዳደር በከተማም ሆነ በገጠር ቀበሌዎች የሰብዓዊነት መዳረሻ ልኬቱ ለአደጋ የማይበገር ትውልድ በመፍጠር መሆኑም በስልጠናው ወቅት ተገልጿል።
ለሚከሰቱ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት የተቀናጀ የሀብት ማሰባሰብና የሴክተር መስሪያ ቤቶች እና የግል ድርጅቶች በጋራ በተቀናጀ መልኩ ተባብሮ የሚሰሩበትን የአሰራር ስልት በጋራ አስቀምጠዋል።
በስልጠናው የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በራስ አቅም የአደጋ ምላሽ የሀገር በቀል የመረረዳት ባህልን ማሳደግ የአደጋ ምላሾችን በራስ አቅም ማድረግ ለግጭት መንስኤ የሆኑ አካባቢዎችን የልማት ተጠቃሚነት በማስፋት የባለድርሻ አካላት እና የሴክተር ተቋሟት ሚና ከፍተኛ ነው ተብሏል።


