ወጣቶች እና ታዳጊዎች ክረምቱን በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ማሳለፋቸው አካላዊ ጥንካሬያቸውን እንዲያጎለብቱ ከማድረጉ በተጨማሪ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማግኘት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተጠቆመ

በድሬዳዋ አስተዳደር የወረዳ 2 ወጣቶችና ስፖርት ማስተባበሪያ አስተባባሪነት የ2017/18 ዓ.ም የታዳጊዎች የክረምት እግር ኳስ ውድድር ማጠቃለያ መርሃ-ግብር ማምሻውን በድምቀት ተካሂዷል።

በዚህም መርሀ-ግብሩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደረጀ ፀጋዬ ወጣቶች ክረምቱን ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ ሰው ተኮር ስራዎች ላይ ተሰማርተው ከማገልገላቸው ጎን ለጎን ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ማድረጋቸው የእርስ በእርስ ወንድማማችነትን እና እህትማማችነትን እንደሚያጠናክረው ገልፀዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገበየሁ ጥላሁን በበኩላቸው ወጣቶች ክረምቱን በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማሳለፋቸው ጤናቸውን እንዲጠብቁ ማስቻሉን እና ይህም ንቁ እና ጠንካራ ሀገር ተረካቢ ወጣትን ለማግኘት እንደሚረዳ አብራርተዋል።

ክረምቱን ወጣቶች በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማሳለፋቸው ከአልባሌ ቦታዎች እንዲርቁ እንደሚያደርግ የተናገሩት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ካሊድ መሀመድ ናቸው።

አቶ ካሊድ አያይዘውም እንደነዚህ አይነት ስፖርታዊ ውድድሮች ተተኪ ስፖርተኞችን ለማግኘት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።

የወረዳ 2 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አቤል ምስራቅ በበኩላቸው ለፕሮግራሙ መሳካት የበኩላቸውን አስተዋፆ ላበረከቱ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በዛሬው የማጠቃለያ መድረክ 47 ታዳጊ ቡድኖች በእድሜ ክልል በሶስት ቡድን ተከፍለው የእግር ኳስ ውድድር ያደረጉ ሲሆን ለአሸናፊዎች ማበረታቻ ሽልማት ተበርክቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *