በድሬዳዋ አስተዳደር የኮሪደር ልማትና የህንፃ ስታንዳርዶች እንዲሁም የቀጣይ የኮሪደር ልማት ምዕራፎችን ለማስተግበር ከሚመለከታቸው ነዋሪዎች፣ የህንፃ ባለቤቶችና ተቋማት ጋር የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
በዚህም በመድረኩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም ግርማይ በኮሪደር ልማት ስራ የተከናወኑና በቀጣይም የሚከናወኑ ስራዎችን ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ የሚያስችል ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በተለይም በኮሪደሩ የሚለሙ አካባቢዎች ላይ ያሉ ተቋማትና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ከተማውን በሚመጥን መልኩ ግንባታና ማሻሻያ እንዲደረግባቸው እተደረገ እንደሚገኝም አቶ ኤፍሬም ጠቁመዋል።
በአጠቃላይም የንግድ፣ የአገልግሎትና መኖሪያ ቤቶች
የመብራት ስታንዳርድ፣ የአጥር፣ የአረንጓዴ ስፍራዎች እንዲሁም የክላዲንግና የቀለም ስታንዳርድ
ተቀምጦላቸው እንዲፈፀሙ እየተደረገ መሆኑንም አቶ ኤፍሬም ጨምረው ገልፀዋል።
እነዚህ ተግባራት ወጥ የሆነና ካለው የአየር ንብረት ብሎም ከስነ-ምህዳር ሁኔታ ጋር የተጣጣመ የግንባታ ሂደት እንዲኖር በማስቻል ዘመናዊና ውብ ከተማ ለመፍጠር ያስችላል ተብሎ የታመነበት
እንደሆነ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
በመድረኩ ከቅንጅታዊ አሰራር፣ ከደንብ ማስከበር ብሎም በአጠቃላይ ለከተማው ልማት በጋራ ከመስራት ጋር በተያያዘ ሰፊ ውይይት ተደርጎ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።
የድሬዳዋ የኮሪደር ልማት ስራ በምዕራፍ ተከፋፍሎ እየተከናወነ ሲገኝ፤ በአጠቃላይ 27 ኪሎ ሜትር በኮሪደር ልማት ለመሸፈን ታቅዷል።


