የድሬዳዋ መምህራን ማህበር የ2ኛ ጠቅላላ ጉባኤ እና የ 37ኛው መደበኛ የምክር ቤት ስብሰባ ማካሄድ ጀምሯል።
በዚህም በመርሃ-ግብሩ የተገኙት የኢትዮጲያ መምህራን ማህበር ተወካይ ወ/ሮ ደብሪቱ ጌታቸው ማህበሩ የመምህራንን መብትና የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅ ባለፈ በሀገራዊ ነባራዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የማህበሩ አባላት ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ እንደሚገኝ የገለፁት ወ/ሮ ደብሪቱ ማህበሩ የእርስ በእርስ ትስስርን የማስፋት ስራ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የድሬዳዋ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ አብዲ ሀቢቤ በበኩላቸው ማህበሩ የመምህራን ጥቅማ ጥቅም መከበር ላይ፣ የትምህርት ጥራት ላይ፣ የህብረተሰብ ተሳትፎ ጉዳይ ላይ እንዲሁም በሀገር ልማት ላይ በስፋት እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ፕሬዝዳንቱ አያይዘውም መምህራን ለትዉልድ ቀረፃና ለሀገር ግንባታ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው አመላክተዋል።
በቀጣይ ማህበሩ የሚሰራቸውን ስራዎች ለማህበረሰቡ የማስተዋወቅ ስራ በስፋት እንደሚሰራ ያመላከቱት ደግሞ የድሬዳዋ መምህራን ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት እና የህዝብ ግንኙነት ተጠሪ የሆኑት መምህር መሀመድ አብዱሌ ናቸው።
መርሃ-ግብሩ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን በከሰዓቱ መርሃ-ግብር 3ኛው የሴት መምህራን ኮኮስ የውይይት መድረክ የሚካሄድ ይሆናል።
በአጠቃላይም በመድረኩ ማህበሩ ያከናወናቸው ስራዎች ሪፖርትና ቀጣይ የስራ አቅጣጫዎች ይቀርባል በተጨማሪም የማህበሩ ተወካይ አመራሮች ምርጫ የሚከናወን ሲሆን በሌሎችም አጀንዳዎች ላይም ውይይት እንደሚደረግ ከወዲሁ ተጠቁሟል።


